˝ጎለጎልታ˝፡- ፍቅር ቤቷን የሰራችበት ኮረብታ

You are currently viewing ˝ጎለጎልታ˝፡- ፍቅር ቤቷን የሰራችበት ኮረብታ

AMN – ሚያዝያ 10/2017


አንዳንድ እጆች አሉ፡፡ ከእውነት፣ ከፍቅር፣ ከሰላም፡ ከአብሮነት ደርሰው የተጣሉ፡፡ ደግሞም አንዳንድ እጆች አሉ ለእውነት፣ ለፍቅር ሁሌ እሚዘረጉ፡፡ አንዳንድ እጆች አሉ፣ በዐዕምሮ ስፋት ልክ ሀሳብን ሸምነው ይህችን እርቃን አለም ወርቀ ዘቦ የሚያጎናፅፉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች አሉ፣ በረቀቀ አዕምሯቸው በንፁህ እጃቸው ድብቁን ቅኔ ፈትተው ነፍስን ከስጋ የሚያስታርቁ፡፡
የሰአሊና የገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ እጆች ደግሞ እጅጉን የሚገርሙ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ˝ጎለጎልታ˝ የተሰኘች ስራው ከበቂ በላይ ምስክር ናት፡፡ ለምን ቢሉ የአለም ጠቢባን ነገረ ስቅለቱን በብዙ መልኩ ገልፀውታል፡፡ ገብረ ክርስቶስ ግን እንደ ስሙ የክርስቶስን ድንቅ ስራ የመሰከረበት ˝ጎለጎልታ˝ የተሰኘ ስራው እፁብ ድንቅ ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳያስ አስቀድሞ በትንቢቱ፡- 53 ÷5 “በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን።” ብሎ እንደተናገረው ሁሌም ነገረ ስቅለቱን ባሰብን ቁጥር በልቦናችን ሰማይ ተስሎ ይታይ ዘንድ ይህንን ድንቅ ምስጢር በደም ሳለው፡፡
ይህ! ዕውቁ ሠዓሊና ባለ ቅኔ የገብረ ክርስቶስ ደስታ “ጎልጎታ” በሚል ርዕስ የተጠበበት የኢየሱስ ክርስቶስ የሥነ ስቅለት አስደናቂና ዘመን አይሽሬ (classical) ሥራው ነው። ገብረ ክርስቶስ ደስታ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ ጥበብ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠቀሱ የጥበብ ፈርጦች መካከል ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የሚሰለፍ የጥበብ ቀንዲል ስለመሆኑም ብዙዎች መስክረውለታል።
˝ከማን ጋር እንደምትውል ንገረኝና ማን እንደሆንክ አውቅሃለሁ˝ እንዲል የሀገሬ ሰው፣ ከልጅነቱ ጀምሮ ከታወቁት የቅኔ መምህርና የተዋሕዶ ሊቅ ከሆኑት ከአባቱ ከአለቃ ደስታ ነገዎ ዘንድ ፊደል ቆጥሮ፣ ዳዊት ደግሞ፣ ዜማ ተምሮ፣ ከጥበብ ጋር የተወዳጀ ነው፣ ገብረ ክርስቶስ፡፡ እናም በአንድ ወቅት በመስቀል ላይ የዋለው ኢየሱስ ክርስቶስን በብሩሹ ብርሃን ሊገልጥ ቀለሙን በጠበጠ፣ ብሩሹን ወደረ፣ ሸራውንም ወጠረ። ቀለሙንም ከሸራው አዛመደ፤ አጣመረ፤ አዋሀደ፡፡ የፍቅርን ቅኔ በብሩሹ አመሰጠረ፡፡ በልቡ ማህሌት ላይ ቆሞ፤ ሸራውን እንደ መቋሚያ፣ ብሩሹንም እንደ ፅናፅል ወዲያና ወዲህ በጥበብ እየወዘወዘ ተቀኘ። ክርስቶስ ለሰው ልጅ የከፈለውን መስዋዕትነት በጥበብ ሲገልፀው በቀራኒዮ አደባባይ ለአለም ሁሉ ቤዛ ይሆን ዘንድ የተሰቀለውን ጌታ በደም ሳለው፤ በፍቅር ገለፀውም፡፡ በጥበብ መሰለው፡፡ እውነትም ገብረ ክርስቶስ!!
ባለ ቅኔውና ሰዓሊው ገብረ ክርስቶስ “ጎልጎታ” ብሎ ስለሰየመው ስራው ሲናገር እግዚአብሔር የሁሉ ፈጣሪ፣ የጥበብ ሁሉ መዝገብ፣ የፍቅር ምንጭ የሆነ- የፍቅር አምላክ ነው!! ሁለንተናው ፍቅር የሆነ፣ በፍቅር የተጥለቀለቀ፣ በፍቅር ስለ ፍቅር የቆሰለ፣ በፍቅር ስለ ፍቅር በደም የተነከረ፣ ደም ግባቱና ውበቱ ደም የጎረፈበት፣ በደም የተረጨ፣ በደም የታተመ፣ በደም የተጥለቀለቀ፣ ሞትን በሞት የረታ ሕያው፣ ዘላለማዊ ፍ-ቅ-ር ነው!! ሲል መስክሮለታል፡፡
ሰዓሊና መምህር አቶ እሸቱ ጥሩነህ፣ በአንድ ወቅት “የገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ አጭር ትውስታና ጨረፍታዊ ዕይታ” በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባቀረቡት ጥናት ላይ እንደገለፁት፣ ሠዓሊ ተብሎ የጎልጎታን ተራራ ያልወጣ፣ የቀራኒዮን ትልቁን ትራጀዲ ያላየ የለም፤ ግን የገብረ ክርስቶስ ሥነ-ሥቅለት ለብቻው ነው። ቀለም ተናጋሪው ነው፣ የሚታየው ንጹሕ ደም ብቻ ነው። ግራና ቀኝ የነበሩት (የተሰቀሉት) እነ ፋይታዊ ቦታ የላቸውም ተዘንግተዋል። ወይም ሠዓሊው ሊያያቸው አልፈለገም፣ ይገርማል። ጥበብ ከንጹሕነት ከጽርየት ከርቀት ብቻ እንጂ ከሌላ ጋር ግንኙነት የሌላት መሆኑን ለመረዳት የሚያስችል እንደሆነም መስክረውለታል።
ዛሬም ድረስ የገብረ ክርስቶስ የፍቅር የነፍሱ ምጥ ውልደት የሆነችው “ጎልጎታ” የፍቅር ሕያው መዝገብ፣ የጥበብ ሥራዎቹ ሁሉ ቁንጮ ሥራ ሆና በዚህ ክብሯ፣ ማዕረጓና ሕያውነቷ ዘልቃለች። ፍቅርን በመሥዋዕትነት፣ ፍቅርን በእውነት፣ ፍቅርን በደም እየተረከች፣ በደም እየሞሸረች፣ በእሾኽ አክሊል፣ በደም እያነገሠች፣ በጦርና በችንካር በደም እያስዋበች፣ በደም እየተረከች።
በዚህ በእጅጉ አስገራሚ፣ አስደናቂና አስደማሚ በሆነው የጥበብ ሥራው ገብረ ክርስቶስ ፍቅርን በጥበብ ቋንቋ፣ በረቂቅ ክህሎት፣ ልዩ በሆነ ኃይል ትላንት፣ ዛሬ፣ ነገም እስከ ዘላለምም ሲያውጅ ታዩታላችኹ፤ ትሰሙታላችኹ፡፡ ሊያውም በለሆሳስ በሆነ የነፍስ ጩኸት፣ የነፍስ ድምፅ፣ የነፍስ ቋንቋ!! በገብረ ክርስቶስ በ”ጎልጎታ” ሥራ ላይ ይህን ታላቅ እውነት፣ ይህን በደም የተከፈለ፣ በደም የጸና የፈጣሪ፣ የአምላክ ፍቅር፣ ምሕረት፣ ይቅርታ፣ በጎነት፣ በረከት፣ ቸርነት፣ ርኅራኄ፣ ፍትሕ፣ ፍርድና ጽድቅ በጉልህ በደም ቋንቋ፣ በደም ቅኔ ይነበባል፣ በጉልህ ይተረጎማል።
መልካም የስቅለትና ትንሳኤ በዓል !


በመለሰ ተሰጋ ከAMN ዲጂታል ሚዲያ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review