ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ተጋላጭ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ብትሆንም የአየር ንብረት ተጽዕኖን ለመከላከል እጅጉን ቁርጠኛ ሆና እየሰራች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ከሰሞኑ በቬትናም ይፋዊ የስራ ጉባኝት ሲያደርጉ የቆዩት የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ዘላቂ እና ህዝብን ማዕከል ያደረገ አረንጓዴ ሽግግር” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የ2025 የፒ ፎር ጂ የአየር ንብረት ጥበቃ ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከሁለት አመት በኋላ የሚካሄደውን 5ኛውን የፒ ፎር ጂ የአየር ንብረት ጥበቃ ጉባኤ ለማዘጋጀት የጉባኤውን ችቦ ከቬትናም ተረክባለች፡፡

በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባደረጉት ንግግርም ጉባኤው የእሳቤዎች ስብስብ ብቻ ሳይሆን አረንጓዴ ልማትን ለማፋጠን፣ ትብብርን ለማጠናከር እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የጋራ ስምምነት የምንደርስበት ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ 5ኛውን የፒ ፎር ጂ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ለማዘጋጀት ቁርጠኛ መሆኗንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ተጋላጭ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ብትሆንም የአየር ንብረት ተጽዕኖን ለመከላከል እጅጉን ቁርጠኛ ሆና እየሰራች መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ የፒ ፎር ጂ ትብብር ማዕቀፍ በጎርጎሮሳውያኑ 2020 ይፋ ከሆነበት ግዜ ጀምሮ እሳቤዎቹ እና አላማዎቹ ከግብ እንዲደርሱ በቁርጠኝነት ስትሰራ መቆየቷን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማዕቀፉ በመንግስት ፖሊሲዎች እና በግሉ ዘርፍ የፈጠራ መፍትሄዎች መካከል አገናኝ ድልድይ ነው ብለን እናምናለንም ብለዋል፡፡
በሰብስቤ ባዩ