ለወገን የተዘረጉ እጆች

You are currently viewing ለወገን የተዘረጉ እጆች

ባለፉት ሰባት ዓመታት በማዕድ ማጋራት 7 ሚሊዮን የከተማዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸው ተገልጿል

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰዎችን ታሳቢ ያደረጉ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን ከውኖ በርካቶችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተለይም የአረጋዊያን ማዕከል፣ ‘ለነገዋ’ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል፣ ተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት፣ የአቅመ ደካማ ቤቶች እድሳትና ግንባታ፣ ገላን ጉራ መንደር፣ ለሚ የእንጀራ መጋገሪያ እና ጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራዎች በርካታ ቁጥር ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ካደረጉ መሠል ስራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

እነዚህ ሀብቶች የሴቶችን፣ የአዳጊዎችን፣ የወጣቶችን፣ የአረጋዊያንን እና የአካል ጉዳተኞችን እንዲሁም በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ህይወት በተጨባጭ እያሻሻሉ ስለመሆናቸው በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጥናት መምህርና ተመራማሪ ጉተማ ኢማና (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት መምህር ጉተማ (ዶ/ር) በማብራሪያቸው፣ ሰዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ማሟላት ሊያቅታቸው እንደሚችል ጠቁመው፣ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ላሉ ወገኖች የከተማ አስተዳደሩ አስገንብቶ ወደ አገልግሎት ያስገባቸው ፕሮጀክቶች ቀላል የማይባል እገዛ ያደርጋሉ፤ የተጠቃሚዎችን መሠረታዊ ፍላጎቶች ከማሟላት አልፈው ገመናቸውን በመሸፈን ስብዕናቸውንም ያስከብራሉ የሚል ነጥብ አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ማዕድ ማጋራትን አስመልክቶ በሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ጉዳዩ አፅንኦት እንዲሰጠው አበክረው ያሳስባሉ። የዘንድሮውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት አማካኝነት በተካሄደው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ተግባሩ ባህል መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በዓል ሲመጣ እጅ አጠር ሰዎች ይሰቃያሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‘ልጆቻችንን ምን እናበላለን? የሰው እጅ ያዩ ይሆን?’ እያሉ የሚያስቡ ወገኖች እንዳሉ አውስተው፣ “ሀብታሞች ደግሞ በተቃራኒው ተርፏቸው ይደፋሉ፤ ስለዚህ ከሚደፋ በየቤቱ ተሳስበንና ያለንን ተካፍለን መኖር እንደሀገር እየዳበረ ከሄደ ኢትዮጵያ ለራሷ መሆን ትችላለች” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ማዕድ የማጋራት ባህል በየሰፈሩ፣ በየተቋሙ፣ በየክልሉና በየጎረቤቱ መዳበር እንዳለበት ጠቅሰው፣ መረዳዳት ብንችል ያጣ ሰው ለዕለት ጉርሱ አይጨነቅም፤ ‘ልጆቼን ምን ላብላ እያለ አይሰቃይም’፡፡ ልጆቿ ሲመኙ አይታ ማጉረስ ያልቻለች እናት ብዙ ትታመማለች፤ ውስጧ ይደማል፡፡ ስለዚህ የተቸገሩትን እምባ ማበስ ባህል መሆን አለበት ብለዋል፡፡

በቅርቡ በብሔራዊ ቤተ መንግስት በተካሄደው ሁለተኛው የኢፍጣር መርሃ ግብር፣ ማዕድ ማጋራት የሀገር ወዳድነት ምልክት፣ የወዳጅነት ውብ ማስታወሻ ነው ብለዋል። አክለውም፣ “ማዕድ ማጋራት አንጡራ ባህላችን ነው። ካለን ላይ እናጋራ፤ ደስታን እንጋራ፣ እርስ በርሳችን እንደጋገፍ፤ በዓሉን በኀብረት ካለችን ለሌለው እያካፈልን ልባችንን እና ነፍሳችንን የሚመግቡ ትውስታዎችን በመፍጠር እናሳልፍ” ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

በሀገራችንም ሆነ በዓለማችን ኃይማኖታዊ እና ማህበራዊ መሰረቶችን መነሻ በማድረግ  በበዓላት ሰሞን ከመደበኛ ቀን ከፍ ባለ መልኩ ተካፍሎ መብላት፣ መረዳዳት እና መደጋገፍ ይስተዋላል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማም በግለሰብ ደረጃ ያለው ለሌለው አካፍሎ በዓሉን በደስታ ማሳለፍ የተለመደ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚያከናውናቸው ሰው ተኮር ስራዎች መካከል አቅም የሌላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የሚደጉምበት የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር አንዱ ነው። በዚህ መርሃ ግብር ባለፉት ሰባት ዓመታት በድግግሞሽ 7 ሚሊዮን የከተማዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን  ከአዲስ አበባ ከተማ የህብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። ሰሞኑንም የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ለ200 ሺህ የከተማዋ አቅመ ደካማ ነዋሪዎች ማዕድ የማጋራት መርሃ ግብር አከናውኗል፡፡

ከንቲባ ጽሕፈት ቤትም በዚሁ ዕለት ለ5 ሺህ ነዋሪዎች ማዕድ አጋርቷል። በመርሃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ ማዕድ ማጋራት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ወገኖች የምንደጉምበት፣ ፍቅራችንን እና አክብሮታችንን የምንገልጽበት ነው ብለዋል። አክለውም፣ በዓልንና አንዳንድ የኑሮ ጫናዎች የሚኖሩበትን ወቅቶች በመለየት ማዕድ ስናጋራ ቆይተናል፤ በ2017 ዓ.ም ብቻ መርሃ ግብሩ 8 ጊዜ ተከናውኗል ብለዋል።

በማዕድ ማጋራትና በሌሎች ሰው ተኮር መርሃ ግብሮች ማህበራዊ ስብራቶቻችን ይጠገናሉ ያሉት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣ “ለድጋፍ ሩቅ አማትረን እጅ ከመዘርጋት ይልቅ መረዳዳቱና መደጋገፉ እርስ በእርስ እንዲሆን፣ ጊዜያዊ ችግሮችን አብረን እንድናልፍ እና  ዘላቂ መፍትሔዎችንም በጋራ ለማፈላለግ የምንተጋ ዜጎች እንድንሆን በማመን ይህንኑ እየተገበርን እንገኛለን” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣ “ሰዎች መተሳሰብ እንዲችሉ ካለን ላይ ማካፈል፣ የተቸገረን፣ የሀገር ባለውለታን፣ ጠያቂና ደጋፊ የሌላቸውን፣ ለማህበራዊ ህይወት ተጋላጭ የሆኑ ወገኖቻችንን አስበናቸው ችግሮችን እያቃለልን አብሮ መኖርን በደንብ ያዳበርንበት ነው የምገባ መርሃ ግብር፡፡ መረዳዳትና መተሳሰብ እንዲኖር ምቹ ሁኔታ መፍጠርም ተችሏል፤ ጫናዎች እንዲቃለሉ፣ የበርካታ ጓዳዎች ገመና እንዲሸፈኑ፣ የዘመሙ ቤቶች እንዲቃኑ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል” ማለታቸውም የሚታወስ ነው፡፡

የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያ አቶ አሕመድ ሰይድ ማዕድ ማጋራትን ጨምሮ ሌሎች በጎ ተግባር በጠቅላይ ሚኒስትር እና በከንቲባ ደረጃ ሲከናወን ለብዙዎቻችን የሚሰጠው ትርጉም ትልቅ ነው ብለዋል። “አንድም ሁላችንም ባለን አቅም ምንም ሳይገድበን መረዳዳት እንዳለብን፤ በሌላ በኩልም በተሰማራንበት ቦታ ሁሉ ለሌሎች ተምሳሌት የሚሆኑ በጎ ነገሮችን ለወገኖቻችን ማድረግ እንደሚገባን ትምህርት ይሰጣል” የሚል ማብራሪያም አክለዋል፡፡

የትንሳኤ በዓል የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ተጠቃሚዎች በበኩላቸው፣ በእንደዚህ አይነት ተግባር አቅመ ደካሞችን መርዳት በዓልን በደስታ እንዲያሳልፉ ያደርጋል ሲሉ  በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በኩል ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

“የዕለት ጉርስ ያጣን ሰዎችን በዚህ መልክ ሰብስቦ መርዳት ቀላል ነገር አይደለም” ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ “የተደረገልን ድጋፍ በዓልን ከቤተሰቦቻችን ጋር በደስታ እንድናሳልፍ ያስችለናል” ብለዋል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመንግስት ደረጃ ሳይቀር ማዕድ ማጋራት፣ በዓላትን አብሮ ማሳለፍና ማህበራዊ ፍትሕን የሚያረጋግጡ ስራዎችን የማከናወን ልምድ እየተስተዋለ ነው፡፡ ይህ ተግባር በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ጎልቶ ይታያል፤ ከ35 ሺህ በላይ የዕለት ጉርስ ያጡ ሰዎች በልተው የሚያድሩባቸው ‘ተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት’ም ተከፍተው የብዙዎችን ችግር እያቃለሉ ነው፡፡

ተማሪዎች ባዶ የምሳ ዕቃ ይዘው ወደየትምህርት ቤታቸው ይሄዱበት የነበረው አስከፊ ታሪክ ተለውጦ ከ835 ሺህ በላይ የሚሆኑት በየትምህርት ቤቶቻቸው በቀን ሁለት ጊዜ የምገባ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ይህም የቀደመ መረዳዳታችን፣ መተሳሰባችን እና አንዳችን ለአንዳችን መቆማችንን የሚመሰክር መሆኑን የጠቆሙት መምህር ጉተማ (ዶ/ር)፣ ተግባሩ መረዳዳትን፣ አብሮ መቆምን ችግርን በጋራ ተካፍሎ ማለፍን የተረዳ ትውልድ ለመገንባት ትልቅ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡

በኃይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላት አንዱ ለሌላኛው ስጦታ የመስጠት ባህል ከጥንት ጀምሮ የነበረና አሁንም ቀጥሎ ያለ ተግባር ነው፡፡ እርስ በእርስ መደጋገፍና መጠያየቅ ወዳጅነትን ያጠነክራል፤ አብሮነትን ያጎለብታል፤ በተለይም በማህበረሰቡ ዘንድ መከባበርና መደጋገፍ እንዲኖር የሚያደርግና ይበልጥም የአንድን ማህበረሰብ የጋራ እሴት የማጠናከር እና የማሳደግ አቅም አለው፡፡

እንደ መምህር ጉተማ (ዶ/ር) ገለፃ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በተለያዩ ኃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት ማዕድ የማጋራት፣ ችግረኞችን የመጠየቅና መደገፍ እንቅስቃሴ ይታያል፡፡ ይህም የማህበረሰቡን ትስስርና መስተጋብር የበለጠ የሚያጎለብት፤ እንደ ሀገርም ትልቅ አቅምን የሚፈጥር ነው፡፡ በተለይም በበዓላት ወቅት ይህ መጠያየቃችን ጠንከር ብሎ ቢታይም እንደ እምነታችን አስተምህሮ በጎነት ዘወትራዊ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን መሰረት በማድረግ ሁላችንም በየእምነታችን አስተምህሮ መሰረት ሁሌም መደጋገፍና መረዳዳት ይገባናል፡፡

የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያ አቶ አሕመድ በበኩላቸው፣ መረዳዳት፣ መደጋገፍ፣ ማዕድ ማጋራትና ስጦታዎችን መሰጣጠት የማህበረሰቡን መስተጋብር የሚያበለፅጉ እና አብሮ ለመኖርም ትልቅ ምሶሶ የሚሆኑ ናቸው ብለው፣ የማህበረሰቡን ትስስርና መስተጋብርም የበለጠ የሚያጎለብት፤ እንደ ሀገርም ለአንድነት ትልቅ አቅም የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይህ በጎ ልምድ በመርሃ ግብሮች ተደግፎ ይበልጥ እርስ በርስ እንድንደጋገፍ እድል ፈጥሯል። ይኸን ተግባር በተለይ በበዓላት ወቅት ማጉላት ፋይዳው ትልቅ በመሆኑ ሁላችንም በምንችለው አቅም ኃላፊነታችንን በመወጣት አብሮነታችንንና አንድነታችንን እናጠናክር ሲሉም መክረዋል፡፡

በተካልኝ አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review