መንግስት የአረንጓዴ ኢነርጂ ኢኒሼቲቮች ተቋማዊ መዋቅር እንዲኖራቸው ለማድረግ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍስሃ ሻውል ገለጹ።
ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን፣ ከኢስት አፍሪካ የማዕድን ኩባንያ እና ሙገር ሲሚንቶ ኩባንያ የተወጣጣ የከፍተኛ አመራር ልዑካን ቡድን ለጉብኝት ህንድ ኒው ዴልሂ ይገኛል።
ልዑኩ በቆይታው በህንድ ያለው የኢንዱስትሪ አሰራሮችን የሚጎበኝ ሲሆን፣ ጉብኝቱ ኢትዮጵያ ለዘላቂ ልማት እና የአረንጓዴ ኢነርጂ ትራንስፎርሜሽን ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጿል።
በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍሰሃ ሻውል ከልዑኩ ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ ከካርቦን ነፃ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት የያዘቻቸውን ግቦች አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የአረንጓዴ ኢነርጂ ኢኒሼቲቮች ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖራቸው በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝም መግለፃቸውን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።