የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ 25ኛውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል የጉራራ ቅርንጫፍ ስራ አስጀምረዋል።
በመርሐግብሩ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የትንሳኤ በዓል እየሱስ ክርስቶስ ያለቀለም ፤ሀይማኖት ፤ እና ቋንቋ ልዩነት ለሰው ልጆች ሁሉ ራሱን አሳልፎ የሰጠበት የፍቅር ምሳሌ ነው ብለዋል።
ይህንን መነሻ በማድረግም የትንሣኤን በዓል ስናከብር መሰል ተቋማቶችን ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር በመገንባት ፍቅራችንን የምንገልጽበት ነው ብለዋል።
አዲስ አበባ አንዳንዶች ለእለት ጉርስ የሚቸገሩባት ሌሎች ደግሞ ምግብ የሚጥሉበት ከተማ መሆኗን የገለጹት ከንቲባዋ ከተማ አስተዳደሩ የደሃውን ማህበረሰብ የኑሮ ሸክም ለማቅለል ከ2014 ዓ ም ጀምሮ ዜጎች በቀን አንድ ጊዜ ንፁህ ምግብ የሚመገቡባቸውን የምገባ ማዕከላት እያስፋፋ እንደሚገኝ አስታውሰዋል፡፡
ማዕድ በማጋራት ማዕከሉን ስራ ያስጀመሩት ከንቲባዋ ድጋፍ ያደረገውንና በቀጣይነት በቋሚነት በማዕከሉ ዜጎችን የሚመግበውን አያት ሪል ስቴትን አመስግነዋል።
የየካ ክፍለ ከተማም ከንቲባ አዳነች አቤቤ እያደረጉ ላሉት ሁሉን አቀፍ የልማት ስራ ሽልማት ሰጥቷቸዋል።
በአፈወርቅ አለሙ