ከትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ያሉት የሳምንቱ ቀናት ስያሜ እና ትርጓሜያቸው

You are currently viewing ከትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ያሉት የሳምንቱ ቀናት ስያሜ እና ትርጓሜያቸው

AMN- ሚያዝያ 13/2017 ዓ.ም

ከትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ያለው ሳምንት የፉሲካ ምሥጢር የተገለጠበት፤ ከግብፅ ወደ ምድረ ርስት ከሲኦል ወደ ገነት መሻገርን የሚያመላክት ሳምንት ስለመሆኑ በመንበረ ፓትሪያርክ ቅድስተ ቅድሳን ማሪያም ገዳም የስብከተ ወንጌል ኃላፊ መጋቢ ሀዲስ ባህረ ጥበብ አዱኛ ይገልጻሉ፡፡

ይኸውም ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ባሕረ ኤርትራን ካሻገራቸው በኋላ ወደ ምድረ ርስት፤ ነፍሳት ደግሞ በክርስቶስ መሪነት ከሲኦል ወደ ገነት መግባታቸውን የሚገልጽ ነው ሲሉ መጋቢ ሀዲስ ባህረ ጥበብ አዱኛ ለኤ ኤም ኤን ደጂታል አብራርተዋል፡፡

በዚህም የሳምንቱ ቀናት በሚከተለው መንገድ ስያሜ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል፡-

ሰኞ- ማዕዶት (መሻገር) የሚባል ሲሆን፣ በዚህ ቀን ነፍሳት በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከሐሳር ወደ ክብር፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሲኦል ወደ ገነት መሻገራቸውን ለማሳየት መሆኑን ያስረዳሉ።

ማክሰኞ- ቶማስ ፤ ቅዱስ ቶማስ በጦር የተወጋ ጎኑን፣ በቀኖት የተቸነከረውን እጁንና እግሩን ካላየሁ አላምንም በማለቱ ክርስቶስም “ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን” ብሎታል።

ቶማስም ያንን ካደረገ በኋላ አመነ፣ ኢየሱስም “ስለ አየኸኝ አመንህን? ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” አለው ቶማስ ትንሣኤውን ስላመነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዕለቱን ቶማስ ብላ ታስበዋለች።

ረቡዕ – አልዓዛር ተብሎ ተሰይሟል፤ አልዓዛር ክርስቶስ ያስነሣው የማርያም እና የማርታ ወንድም ነው፤ አልዓዛር መጋቢት 17 ሞቶ ክርስቶስ ግን በ4ኛው ቀን መጥቶ ከሞት አስነሥቶታል በዚህም ዕለቱ አልዓዛር ተብሏል፡፡

ሐሙስ- አዳም ፤ ክርስቶስ በተነሳበት አምስተኛው ቀን ሐሙስ፣ አዳም ይባላል፤ አዳምና ሔዋን በገነት 7 ዓመት ከቆዩ በኋላ ትእዛዙን በመተላለፋቸው ከኤደን ገነት አስወጣቸው “ብዙ ተባዙ” ያለው ቃል እንዳይቀር በምድር ላይ ወርደው ልጆችን ወልደዋል፤ ጌታም አዳምን ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ባለው ቃል መሰረትም፣ አዳም ከነልጆቹ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻ ስለመውጣቱ ይታሰብበታል በማለት መጋቢ ሀዲስ አብራርተዋል፡፡

ዓርብ- ቤተ ክርስቲያን፤ ዓርብ የእግዚአብሔር ቅድስት ማደሪያ በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ተሰይማለች፤ ይህም ሁሉም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመባት ዕለት በመሆኗ ነው፡፡

ቅዳሜ- ቅዱሳት አንስት( የሴቶች ቀን)፤ ቅዳሜ ቅዱሳት አንስት ተብሎ ይጠራል፤ ይህም ስያሜ በስቅለት ዕለት በልቅሶና በዋይታ የሸኙትን፤ በዕለተ ትንሣኤ ሽቱና አበባ ይዘው ወደ መቃብር የገሰገሱትን፤ ከሁሉም ቀድሞ ክርስቶስ በዕለተ ሰንበት ተነሥቶ ለተገለጸላቸው ማርያም መግደላዊት፤ የታናሹ ያዕቆብ እና የዮሳ እናት ማርያም፤ የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ሰሎሜንም መታሰቢያ ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እሑድ-ዳግም ትንሣኤ፤ “ያም ከሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን ስለ ፈሩ ተሰብስበው የነበሩበት ቤት ደጁ ተቆልፎ ሳለ ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ብሏቸዋል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ተሰውሮ ከሰነበተ በኋላ በዕለተ እሑድ በዝግ ቤት እንዳሉ ዳግም ተገለጸላቸው፤ስለዚህም ዳግም ትንሣኤ ተባለ በማለት መጋቢ ሀዲስ ባህረ ጥበብ አዱኛ አብራርተዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review