የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያሥላሴ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች ጋር የወንጀል ፍትሕ አሰተዳደር ውጤታማነት ለማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ ባለፉት ዓመታት በጋራ በተከናወኑ የወንጀል ምርመራ፣ ክስና ክርክር ተግባራት አጥፊዎችን ተጠያቂ በማድረግ ረገድ አመርቂ ውጤቶች የተገኙ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች የታዩ ጥንካሬዎችን አጠንክሮ ማስቀጠል ውስንነቶችን በመቅረፍ ጠንካራ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ስርዓት ለመገንባት በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡
የጋራ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት፣ የወንጀል መረጃ ስርዓት ማዘመን፣ የምርመራ ስራዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማስደገፍ፣ የጋራ ዕቅድ ክትትልና ግምገማ ስርዓት መዘርጋት እንዲሁም በየደረጃው ቅንጅታዊ አሠራር ማጠንከር በውይይቱ መግባባት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
በውይይቱ የፍትሕ ሚኒስቴር እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች መሳተፋቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።