ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ከተሞቻችንን የማዘመን ሰፊ ጥረት አይነተኛ ማሳያ የሆነውን በካዛንቺስ ያለዉን የኮሪደር ልማት ክፍል በይፋ መርቀናል ብለዋል።
የተጎሳቆሉ እና በእጅጉ የተጎዱ ቤቶች እና ከባቢ መገኛ የነበረው ካዛንቺስ ዛሬ የጋራ ጥረት እና ለውጥ ሽልማታችን ሆኖ ተገኝቷል ሲሉም አክለዋል።
ከዚሁ አካባቢ ተነስተው ለማኅበረሰባችን የከበረ የኑሮ ሁኔታን ለመፍጠር ያለንን ፅኑ እምነት እና ተግባር በሚያሳይ አኳኋን ለኑሮ ወደ ተሻለ ከባቢ የተዛወሩትን ነዋሪዎች ከጥቂት ቀናት በፊት ጎብኝተን ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የተዛወሩበት ከባቢ እጅግ ምቹ መሆኑን ማየታቸውን ገልጸዋል።
ዛሬ ደግሞ የተነሱበትን ሰፈር ድንቅ የኮሪደር ልማት ሥራ መርቀናል ነው ያሉት።
በአስደናቂ አጭር ጊዜ የተጠናቀቀው የካዛንቺስ ለውጥ ለዘመነ ከተማ ልማት ሥራችን ለአረንጓዴ፣ ንፁህ እና ዘመናዊ የከተማ ማዕከላት ያለንን ርዕይ ግዘፍ ነስቶ በማሳየት መሠረት የሚጥል ነው ሲሉም አመላክተዋል።
በዚህ ግዝፈት የሚከወኑ ሥራዎች ሰፋ ያለ ጥረት ይሻሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጊዜያዊ ምቾት የሚነሱ ፈተናዎችንም ሊያስከትሉ እንደሚችሉ በመግለፅ፣ ነገር ግን ለታላቁ የሀገር ጥቅም የሚከፈሉ አስፈላጊ መስዋዕትነቶች ናቸው ብለዋል።
ይኽ የእድገት መንገድ መቀጠል ያለበት ነው፤ የታደሰ ተስፋ ይሰጣልና በተለይ ለልጆቻችን ነገ በማለትም ነው የገለጹት።