ባለፉት 9 ወራት ከ2 ሚሊየን 10 ሺህ በላይ አሽከርካሪዎችና እግረኞች የትራፊክ ህግና ደንብ መተላለፋቸዉን እና ከነዚህ መካከል 37ሺህ ያህሉ እግረኞች መሆናቸዉን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አማረ ታረቀኝ ገልጸዋል፡፡
በትራፊክ ደንብ መተላለፍ ቀዳሚዎቹም የትራፊክ ምልክትና ማመላከቻዎችን አለማክበር፣ የመንገድ ትራፊክ መብራት መጣስ፣ ከተፈቀደው ፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር፣ ጠጥቶ ማሽከርከር፣ የደህንነት ቀበቶ አለማሰር እና ሄልሜት አለማድረግ መሆናቸዉን አንስተዋል፡፡
የእግረኛ መሰረተልማት በተሟላባቸዉ ቦታዎች እግረኞች መንገዳቸውን በአግባቡ ባለመጠቀማቸዉ በገንዘብ መቀጣታቸውና ማህበራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉንም አስረድተዋል፡፡
የትራፊክ ቁጥጥሩን በቴክኖሎጅ ከማዘመን ጋር በተያያዘም ባለ ስልጣን መ/ቤቱ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ግዜ አዉቶማቲክ ኢንፎርስመንት እና ፓርኪንግ ማኔጅመንት ሲስተምን አልምቶ ባለፉት ወራቶች ወደ ስራ በማስገባቱ ከ1ሚሊየን 24 ሺ በላይ መንጃ ፈቃድ ሲስተም ቋት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
በእዚሁ ሲስተም አሰራር የደንብ ተላላፊዎች ሰሌዳ ሳይፈታና መንጃ ፈቃድ ሳይወሰድ በስልካቸው በአጭር መልእክት እንድያዉቁት ስለሚደረግ በተለያዩ የክፍያ አማራጮች እንዲከፍሉ የሚያስችል መሆኑን መግለጻቸዉን ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል፡፡