በመዲናዋ በ2017 በጀት ዓመት በ9 ወራት ውስጥ ከ259 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በቋሚነት የስራ ዕድል መፈጠሩን የአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የክፍለ ከተሞች እና የወረዳዎችን የ9 ወራት እቅድ አፈፃፀምን እየገመገመ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ፣ ቢሮው በበጀት ዓመቱ ከ3 መቶ ሺህ ለሚልቁ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር እቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
በዚህም ባለፉት 9 ወራት 259 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች በቋሚነት የስራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል ::
48 በመቶ የሚሆኑት ተደራጅተው የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ናቸው ያሉት የቢሮ ኃላፊው፣ 52 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በቅጥር የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ናቸው ብለዋል፡፡
ለወጣቶቹ የስራ ዕድል የተፈጠረውም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአገልግሎት እና በሌሎች ዘርፎች እንደሆነም ተጠቅሷል።
በበጀት ዓመቱ ከ211 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አጫጭር ስልጠናዎች መሰጠታቸውም ተመላክቷል
ቴዎድሮስ ይሳ