በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የተመራው ከፍተኛ ልዑክ እየተካሄደ ካለው የ2025 የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የአለም ባንክ የጸደይ ስብሰባዎች ጎን ለጎን ከአለም ባንክ ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዝዳንትና የምስራቃዊ እና ደቡባዊ አፍሪካ ሃላፊ ከሆኑት አሚት ዳር ጋር ተገናኝቶ ውጤታማ ውይይት አድርጓል።
ሁለቱም ወገኖች በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ታሪካዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ እንዲሁም በቀጣይ ተባብረው በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሃሳብ ተለዋውጠዋል።
ፈታኝ የሆኑ አለማቀፋዊ ሁኔታዎች ቢኖሩም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚነት ማዕከል በማድረግ እየተከናወነ ስላለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና እያስገኛቸው ስላሉት ስኬቶች ሚኒስትሩ ገለጻ ሰጥተዋል።
ሁለንተናዊ ብልፅግና በማምጣት ረገድ የአገሪቱ የገንዘብ ስርዓት ችግርን የመቋቋም አቅም፣ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት፣ ቀጠናዊ ንግድና ትስስር፣ ኢኮኖሚያዊ አካታችነትና ሰብዓዊ ሀብት ላይ ትኩረት አድርጎ እየተሰራበት ስላለው የኢትዮጵያ እድገት ስትራቴጂ አብራርተዋል።
ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዝዳንቱም ኢኮኖሚውን ከማዘመን፣ ግሽበትን ከመቆጣጠር፣ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ከማስፋፋት፣ ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር መጠነ ሰፊ አገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያን እውን ለማድረግ የተወሰዱ ቁርጠኛ የፖሊሲ እርምጃዎችን አድንቀዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር ፐብሊክ ኢንቨስትመንትንና የግሉን ዘርፍ በመደገፍ፣ ፖሊሲ በማሻሻል ረገድ አገሪቱ እያከናወነች ያለችውን ዘላቂ ሁለንተናዊ ዕድገትና ልማት ለመደገፍ ባንኩ ያለውን ቁርጠኝነት መግለፃቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።