ለስደትና ፍልሰት ዘላቂ መፍትሄ ለመፍጠር ቀጠናዊ ትስስርን እና ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስደትና ፍልሰት ጥናት ማዕከል ከዓለም አቀፉ ቀጠናዊ ዘላቂ መፍትሄ ሴክሬታሪያት ተቋም ጋር በመተባበር “በግዳጅ ስደትና ፍልሰት ላይ የደቡባዊው ዓለም ዕይታ በፖሊሲ፣ ምርምርና ትግበራ ጥምርታ አንጻር ሲቃኝ” በሚል መሪ ሐሳብ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በስካይ ላይት ሆቴል፣ አዲስ አበባ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
ከካናዳ፣ ከምስራቅ አፍሪካ እና ከ19 የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ የዘርፉ ምሁራን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የልማት አጋሮች፣ ፖሊሲ አውጭዎችና አስፈጻሚዎች የተሳተፉ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሰዎች መፈናቀል እና ስደት ላይ ያተኮሩ ምርምሮች፣ ፖሊሲዎች እና ተፈጻሚ የሚሆኑ ስልቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በቀጠናው ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች መኖራቸውን ጠቅስው ይህን መሰል መድረክ መዘጋጀቱ መፍትሄዎች ላይ ለመወያየት ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።
የስደትና የፍልሰት ችገሮችን ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ስራዎች እንደሚጠበቁ የገለፁት ተሳታፊዎች ለስደትና ፍልሰት ዘላቂ መፍትሄን ለመፍጠር ቀጠናዊ ትስስርን እና ትብብርን ማጠናከር ይገባል ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
በጉባኤው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝደንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)፣ የዩኒቨርሲቲው የስራ ሀላፊዎች፣ የኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን፣ በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ጆሹዋ ታባህን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል፡፡