የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት ከፍ ለማድረግ በተሠሩ ስራዎች የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም እያደገ መምጣቱን የአዲስ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው በበጀት ዓመቱ 9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ላይ ውይይት አካሂዷል።
በአዲስ አበባ ከኢንዱስትሪዎች ፍላጎት ጋር የተጣጣመና በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፍ አገልግሎት በመሰጠቱ የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም እያደገ መምጣቱም በውይይቱ ላይ ተመላክቷል።
የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት ከፍ ለማድረግ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ ኢንዱስትሪዎችን ለመፍጠር በተሰሩ ስራዎች ባለፉት 9 ወራት ብቻ 31 አዳዲስ ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት መላክ መጀመራቸው ተነግሯል።
ምርቶ ቻቸውን ወደ ውጭ ከላኩ ሀገራትም 132 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የፋሲሊቲና የካይዘን ትግበራ ዘርፍ ሃላፊ ኤፍሬም ግዛው (ዶ/ር) ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ወደ 64 በመቶ ማደጉንም ኃላፊው አብራርተዋል።
የሀገር ውስጥ ምርታማነትን ለማሳደግና ኢንዱስትሪዎች የሚያነሷቸውን አስተዳደራዊ ችግሮች በፍጥነት ለመፍታት በትኩረት ስለመሰራቱም በውይይቱ ላይ ተመላክቷል።
በካሳሁን አንዱዓለም