ኢትዮጵያ የሳይበር ደኅንነት እና ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ የሚያስችል ብቁ እና ዘመናዊ ተቋም መገንባት መቻሏን መመልከቱን የሞሮኮ ሮያል አርሚ ከፍተኛ ልዑክ ገለጸ፡፡
በሞሮኮ ሮያል አርሚ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ በሪድ የተመራ የሞሮኮ ሮያል አርሚ ከፍተኛ ልዑክ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ጉብኝት አድርጓል።
የአሥተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ፣ የኢትዮጵያን የሳይበር ደኅንነት በማረጋገጥ በኩል ተቋማቸው በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል ልማት እና በአሠራር ሥርዓት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አብራርተዋል፡፡
በቀጣይም የሀገራቱን የሳይበር ደኅንነት በማረጋገጥ ረገድ ሁለቱ ተቋማት በጋራ በሚሠሩባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡
ልዑኩ በበኩሉ፣ ኢትዮጵያ የሳይበር ደኅንነት እና ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ የሚያስችል ብቁ እና ዘመናዊ ተቋም መገንባት መቻሏን መመልከቱን ገልጿል፡፡
ጉብኝቱ ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ በዲፕሎማሲው መስክ ያላቸውን ወዳጅነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እና በሳይበር ደኅንነት መስክም ይሁን በሌሎች መስኮች በጋራ ለመስራት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡
ልዑኩ በጉብኝቱ ወቅት፣ የተቋሙን ምርትና አገልግሎቶች፣ የሳይበር ታለንት ልማት ማዕከል እንዲሁም ሌሎች ሥራዎችን መመልከቱን ከአስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡