በጠንካራ ተቋማዊ ሪፎርም እየተገነባ ያለው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ወደ ተሟላ ዘመናዊ የአቪዬሽን ተቋም ደረጃ ማደግ ችሏል ሲሉ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።
ዋና አዛዡ በመከላከያ አዛዥነት እና ስታፍ ኮሌጅ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ከሚገኙ የክፍለ ጦር አመራሮች ጋር በአየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ተገናኝተው ውይይት አደርገዋል።
በውይይቱም ላይ እንደገለጹት ጠንካራ ተቋማዊ ሪፎርምን መነሻ አድርጎ የተነሳው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአመራሩ ጀምሮ እስከ ታችኛው አባላት ደረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለለውጥ ዝግጁ ሆነው በጋራ በመስራታቸው ምክንያት ወደ ተሟላ ዘመናዊ የአቪዬሽን ተቋም ደረጃ አድጓል።
ውስጣዊ አንድነቱ የጠነከረ ብሎም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚችል ሙያዊ አቅም ያለው ሰራዊት እንደ ተቋም መገንባቱን የጠቀሱት ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በ2022 ከአፍሪካ ተመራጭ የአቪዬሸን ተቋም ለማድረግ ከያዝናቸው ውጥኖች መካከል አንዳንዶቹ ቀድመው እየተሳኩ ነው ብለዋል።
ጠንካራ ወታደራዊ መሪ ማለት በሰላም ጊዜ ሰራዊቱን ለውጊያ የሚያዘጋጅና በአነስተኛ ኪሳራ ትልቅ ድል የሚያመጣ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የክፍለ ጦር አመራሮችም የዘመኑን ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ መከተል እንዳለባቸው እንዲሁም የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ያገናዘበ አቅም ደረጃ ላይም ራሳቸውን ለማብቃት ሊተጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ምክትል አዛዥ ለስልጠና ዲን ኮሎኔል ዮሐንስ መኮንን አመራሮቹ የአየር ኃይልን የስኬት ጉዞ እንደ መልካም ተሞክሮ እንደሚወስዱና ለሀገራዊ አላማ ተናበው እንዲሰሩ የሚያስችል ገንቢ ምክረ ሀሳብ ከአየር ኃይል አዛዡ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በዕለቱ የክፍለ ጦር አመራሮች በተቋሙ እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የግዳጅ አፈፃፀም ተግባራትን ተዘዋውረው መመልከታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡