የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሞሮኮ የሮያል ጦር ኃይል ኢንስፔክተር ጄኔራልና የደቡባዊ ዞን ጦር አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ባሬድ የተመራ ልዑክን ተቀብለው አነጋግረዋል።
በ1955 ዓ.ም አካባቢ በይፋ የተጀመረው የኢትዮጵያና ሞሮኮ ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በፓን አፍሪካዊ መንፈስ እና ለአህጉራዊ አንድነት የጋራ ቁርጠኝነት የታየበት ወሳኝ ወቅት እንደነበር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ አስታውሰዋል።
ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ እና በራባት የተካሄደው የከፍተኛ ደረጃ ወታደራዊ ልዑካን ምክክርም ሁለቱ ሀገሮች በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ጉዳዮችን እንዲፈትሹ እድል ፈጥሮላቸው እንደነበር ተገልጿል።
የሞሮኮ ሮያል ጦር ኃይል ኢንስፔክተር ጄኔራልና የደቡባዊ ዞን ጦር አዛዥ ሌተናል ጄነራል ሞሐመድ ባሬድ በበኩላቸው፣ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃነት ምልክት መሆኗንና ወታደራዊ ትብብሩም ለአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ለምናበረክተው አስተዋፅኦ የጎላ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ የአፍሪካ ቀጠና የሚገኙ መሆናቸውን የገለፁት የመከላከያ ውጪ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ በየቀጠናቸው ከሚያበረክቱት አስተዋፅኦ በተጨማሪ በጋራ ለአፍሪካ ሰላምና ደህንነት እንዴት በትብብር መስራት እንዳለባቸውና ምን ምን ጉዳዮች ላይ መተባበር እንዳለባቸውም ውይይት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ከሞሮኮ ወታደራዊ ተቋማት በቴክኖሎጂ ሽግግር ፣ በሳይበር ፣ በአየር ኃይል እና በባህር ኃይል ኢትዮጵያ የምትወስደው ተሞክሮ እንዳለ የገለፁት ጄነራል መኮንኑ ኢትዮጵያ አሁን ላይ በኢንዱስትሪ እያሳየችው ካለው እምርታ አንፃር ደግሞ እነሱም አብረውን እንደሚሰሩና መጪውን ሁኔታ ያገናዘበ ልምድና ተሞክሮ በመለዋወጥ በቀጠናው በሚኖሩ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮችም አብሮ ለመስራት የሚያስችል ውይይት መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በቀጣይ የመግባቢያ ስምምነት እንደሚፈራረሙ ተነግሯል፡፡ ውይይቱን ተከትሎ የልዑካን ቡድኑ በሆሚቾ አሙኔሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪና በአየር ኃይል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን መጎብኘታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡