‹‹የማስተር ሄኖክ በ90 ቀናት ሁለንተናዊ ለውጥ ማዕከል›› ከአዲስ አበባ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር በመጪው ሐሙስ በእንጦጦ ፓርክ የተራራ መውጣት ውድድር እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡
መነሻውን ከቁስቋም ቤተ ክሪስቲያን በሚያደርገው የ5 ኪሎ ሜትር ውድድር ላይ ከ10 ሺ በላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አዘውታውሪዎች እንደሚሳተፉ አዘጋጆቹ አሳውቀዋል፡፡
ውድድሩን ለማካሄድ እቅድ የተያዘው ከወራት በፊት ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ሲራዘም መቆየቱን የማስተር ሄኖክ በ90 ቀናት ሁለንተናዊ ለውጥ ማዕከል መስራች ማስተር ሄኖክ ኪዳነ ወልድ ጠቁሟል፡፡
በውድድሩ ላይ የሚሳተፉት፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያዘወትሩ ይሆናሉ ብሎ እንደሚገምት የገለጸው ማስተር ሄኖክ፣ ከውድድሩ በፊትም ሆነ በኋላ መደረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ከአዘጋጆቹ መልዕክት እንደሚተላለፍም ተገልጧል፡፡
ሚያዝያ 23 2017 ማለዳ ይካሄዳል የተባለው መርሃ ግብር ከውድድር በተጨማሪ የመዝናኛ አማራጮችን እንደሚያካትትም ነው የተጠቆመው፡፡ ተራራ የመውጣት ውድድር እንዳልተመደ የሚጠቅሰው ማስተር ሄኖክ፣ ውድድሩን ከአዲስ አበባ ባሻገር በሁሉም ክልሎች የማዘጋጀት እቅድ እንዳለውም አስታውቋል፡፡
ሐሙስ ማለዳ የሚካሄደውን ተራራ መውጣት ውድድር ለሚያሸንፉ ተወዳዳሪዎች ሜዳሊያና የማበረታቻ ገንዘብ ሽልማት እንደተዘጋጀም ነው ‹‹የማስተር ሄኖክ በ90 ቀናት ሁለንተናዊ ለውጥ ማዕከል›› የጠቆመው፡፡
በታምራት አበራ