ህይወትን የቀየረው ‘እንጀራ’

You are currently viewing ህይወትን የቀየረው ‘እንጀራ’

     “ጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራዎች ዘላቂ የስራ ዕድል ፈጥሮልናል፤ ገመናችንንም ሸፍኖልናል

                                                                                                             ወይዘሮ አየለች ደበሮ  

በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 1 ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አየለች ደበሮ ለበርካታ ዓመታት ቅጠል ለቅመውና እንጨት ሰብረው በመሸጥ መራራ ህይወትን ገፍተዋል፡፡ ከሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ይህን የህይወት ውጣ ውረድ የተጋፈጡባቸውን ዘመናት በቁጭት ያስታውሷቸዋል፤ ከፍተኛ ክብደት ያለውና የሚቆረቁር እንጨት በጀርባቸው ተሸክመው ከእንጦጦ ተራራ በማውረድ በከተማዋ አዙረው በመሸጥ ቤተሰባቸውን ሲያስተዳድሩ ኖረዋል፡፡ ይህም የማይሽር ጠባሳ እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ አየለች አሁን በጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራዎች በተፈጠረላቸው የስራ ዕድል የተሻለ ህይወት እየመሩ እንደሆነ ገልፀውልናል፡፡ “ልጅ ለማስተማርና ሌሎች ወጪዎች ለመሸፈን እንጨት ተለቅሞ የሚገኘው ገቢ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ሰው ቤት ተመላልሼ ልብስ እስከማጠብ ደርሻለሁ” የሚሉት እኝህ እናት በጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራዎች ውስጥ የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸው የነበረባቸውን ድካምና ጫና እንዲሁም ስጋት እንዳስቀረላቸው ገልፀዋል፡፡

“ጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራዎች ዘላቂ የስራ ዕድል ፈጥሮልናል፤ ገመናችንንም ሸፍኖልናል፤ ደህንነቱ በተጠበቀ ስፍራ እየሰራን እንውላለን፣ ብንታመም የምንታከምበት፣ ቢደክመን የምናርፍበት ቢርበን ምሳችንን እዚያው የምንመገብበት የስራ እድል ተፈጥሮልናል” ብለው ከዚህ በተጨማሪ በወር 1 ሺህ 500 ብር ገቢ እንደሚያገኙ ነግረውናል፡፡

ምንም እንኳን ወርሃዊ ክፍያቸው መጠነኛ ቢሆንም በዚህ ስፍራ በመስራታቸው ህይወታቸው ላይ መሻሻል ማምጣቱን እንደሚከተለው ያስረዳሉ፤ “ከሰዎች ጋር በጋራ መስራት እንዴት እንደሚቻል? ማህበራዊ ህይወትን እንዴት ማስቀጠል እንደሚቻል ትምህርት ከመውሰዴም ሌላ በርካታ ጓደኞችና ወዳጆች አፍርቼበታለሁ” ብለው፣ ከመሃላቸው አንድ እናት ብትታመም ወይ ብትወልድ እንዲሁም ሃዘንም ሆነ መከራ ቢያጋጥማት የመጠያየቅ ጠንካራ ባህል መገንባታቸውንም አንስተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ሽሮ ሜዳ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ተገንብቶ ወደ አገልግሎት የገባው ጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራዎች የበርካታ ዜጎችን ህይወት ስለማሻሻሉ በስፍራው ተገኝተን ባደረግነው ቅኝት ለመገንዘብ ችለናል። በአካባቢው በእንጨት ለቀማና በአስቸጋሪ ስራ ተሰማርተው ለነበሩ ወገኖች የተላለፈው ጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራዎች የእንጀራ ፋብሪካ፣ የጋራ መኖሪያ መንደር፣ የከብት እርባታ፣ የጓሮ አትክልትና የከተማ ግብርና ስራዎች፣ የምገባ ማዕከል እንዲሁም ለአካባቢው ነዋሪዎች ግልጋሎት የሚሰጥ የመንገድ ዝርጋታን ያካተተ ነው፡፡

ከአምስት መቶ ለሚበልጡ ወገኖች የስራ እድል የፈጠረው ይህ ተቋም በዋናነት ከእንጦጦ ጫካ እንጨት ለቅመው በመሸጥና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ወገኖችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፣ እነኚህ እናቶች በክፍለ ከተማው ወረዳ 1፣ 2፣ 3፣ 4 እና 6 ነዋሪና ከ10 እስከ 20 ዓመት ለሚሆን ጊዜ እንጨት በመልቀም በአስቸጋሪ ህይወት ውስጥ የነበሩ መሆናቸውን ከጉለሌ ክፍለ ከተማ የኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራዎች ከአድካሚና አሰልቺ የህይወት መስመር አውጥቶ በተረጋጋና በሰላማዊ መንገድ ህይወታቸውን ለመምራት እንዳስቻላቸው በስፍራው በእንጀራ ጋገራ ስራ የተሰማሩ እናቶች ይናገራሉ፡፡ ልክ እንደ ወይዘሮ አየለች ደበሮ ሁሉ ሌሎች ተጠቃሚዎችም በህይወታቸው መሻሻሎች መምጣታቸውን ገልፀዋል፡፡ ሌላዋ የጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራዎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ ወይዘሮ በለጥሻቸው ፀጋዬ ናቸው፡፡ በቀደሙት ጊዜያት ቤተሰባቸውን የሚያስተዳደሩት ከእንጦጦ ጫካ ቅጠልና እንጨት ለቅሞ በመሸጥ ስራ እደነበር አስታውሰው፣ በጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራዎች በእንጀራ ጋገራ ስራ ከተሰማሩ ወዲህ የተረጋጋ ህይወት ለመምራት መቻላቸውን ገልፀዋል።

የእንጨት ለቀማ ስራ ለልጆች እናት ይቅርና ለማንኛዋም እንስት አድካሚ፣ ውጣ ውረድ የበዛበትና ለአስጊ ሁኔታዎች የሚያጋልጥ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዋ ይህን ችግራቸውን የተመለከተው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራዎችን በማቋቋሙ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። “ከአድካሚና አሰልቺ ህይወት አውጥቶ በተረጋጋና በሰላማዊ መንገድ ኑሮዬን ለመምራት አስችሎኛል” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

እንደ ድሮው ቅጠልና እንጨት የሚሰበሰብበት ማዳበሪያና ገመድ ይዞ ረጅም መንገድ በእግር መኳተን ቀርቶ እንደማንኛዋም የተሻለ ስራ እንደምትሰራ እናት ንፁህ ለብሰው ቦርሳ ይዘው ከቤታው በመውጣት ስራቸውን ሰርተው መመለሳቸው በራሱ ከፍተኛ የአእምሮ እርካታ እንዳው ነው የነገሩን፡፡

ከተፈጠረላቸው የስራ አድል በተጨማሪ፣ “ልጆቼን ምን ላብላ? እንዴት ላስተምር?” ሳይሉ በቀን ሁለት ጊዜ የምገባ አገልግሎት እያገኙ በመንግስት ትምህርት ቤቶች መማራቸው መንግስት የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

የአራት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ አማረች ሸኖ በበኩላቸው፣ በእንጨትና ቅጠል ለቀማ ተሰማርተው በርካታ ዓመታትን ቢያሳልፉም በኑሯቸው ላይ ጠብ የሚል ነገር አለማግኘታቸውን አስታውሰው፣ በጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራዎች ተጠቃሚ መሆናቸው ትልቅ ተስፋ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡ “ከአንድም ሁለት ጊዜ በጅብ ከመበላት ድኛለሁ” የሚሉት እኝህ እናት፣ የእንጨት ለቀማ ስራ ማልዶ መውጣትን የሚጠይቅ በመሆኑ ሁለት ጊዜ ከጅብ መንጋ ጋር ፊት ለፊት ተፋጥጠው በሰዎች እገዛ መትረፋቸውን ነግረውናል፡፡

ይህ ብቻም ሳይሆን ነፍሰ ጡር ሆነው የእለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን እንጨት ለቀማ ያለማቋረጥ ረጅም የእግር ጉዞና ሸክም በማብዛታቸው ፅንስ እስከመቋረጥ የደረሰ ከባድ ችግር ገጥሟቸው እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን በጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራዎች ተጠቃሚ መሆናቸው ያለፈ ችግራቸውን እንደሚያስረሳቸው ገልፀዋል፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ የኮሚኒኬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አንተነህ ለታ እንደገለፁት፣ ክፍለ ከተማው ካለው ተፈጥሯዊ አቀማመጥ አንፃር በርካታ እናቶች ከእንጦጦ ጫካ ቅጠልና እንጨት ለቅመው በመሸጥ ብሎም ከፍተኛ ጉልበት በሚጠይቁ አድካሚ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ህይወታቸውን የሚመሩ ነበሩ፡፡

የሴቶችንና የእናቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የከተማ አስተዳደሩ 5 ነጥብ 6 ሄክታር በሚሸፍን ቦታ ላይ ያረፈ ጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራዎችን የዛሬ ዓመት አከባቢ ስራ አስጀምሯል፡፡ በእንጨት ለቀማ ስራ ሲቸገሩ የኖሩ እናቶችን ህይወት ለመታደግ ታስቦ የተቋቋመው የእንጀራ ማዕከል በእንጀራ መጋገር የተሰማሩ እናቶች ልጆቻቸውን በቅርበት እየተከታተሉ ስራቸውን መስራት ብቻ ሳይሆን ልጄን ምን ልመግብ ብለው ከመጨነቅም ታድጓቸዋል ብለዋል።

አጠቃላይ ፕሮጀክቱ በዋነኛነት በአካባቢው እንጨት በመልቀም ለሚተዳደሩ ከ500 ለሚበልጡ እናቶች የስራ ዕድል ፈጥሯል ያሉት አቶ አንተነህ፣ 450 ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች የተሟሉለት ነው ብለዋል።

እንደ አቶ አንተነህ ማብራሪያ፣ በጉለሌ የእንጀራ ማዕከል የስራ እድል የተፈጠረላቸው እናቶች በሁለት ፈረቃ ተከፍለው እየሰሩበት ሲሆን፣ ሁለት የእንጀራ መጋገሪያ ህንጻዎች፣ የህጻናት ማቆያ፣ በማዕከሉ የስራ እድል ለተፈጠረላቸው ዜጎች አገልግሎት የሚሰጥ የምገባ ማዕከል  የእህል ማከማቻና ወፍጮ ቤት፣ ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላትን ያካተተም ነው። ይህ ማዕከል በእንጀራ መጋገር ብቻ ሳይሆን የጥበቃ ሰራተኞችና ጤፍ የሚያበጥሩትን  ጨምሮ ለ533 እናቶች የስራ እድል ፈጥሯል፡፡

በ1 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን የማልማት ስራ እየተከናወነ ሲሆን የጋራ መኖሪያ ቤቱ ለ200 አባዎራዎች እና እማወራዎች ተዘጋጅቶ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ተሟልቶለት የተሰራ ነው፡፡ በከብት እርባታ በአራት ማህበራት የተደራጁ 40 ወጣቶች ተጠቃሚ ሲሆኑ ለእነኝህም 47 የወተት ላሞች እና ሌሎች ግብዓቶች ተሟልተውላቸው አሁን ላይ ውጤታማ ስራ እየሰሩ እንደሆነ ነው ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ያገኘነው መረጃ የሚያመላክተው።

በሸዋርካብሽ ቦጋለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review