ዓለማችን በየጊዜው የተለያዩ የመኪና ዓይነቶችን ጥቅም ላይ በማዋል ውድድር ውስጥ በገባችበት በዚህ ዘመን መኪና ማሽከርከር ክልክል የሆነበት የአሜሪካ ደሴት መኖሩ አስገራሚ ሆኗል፡፡
መኪና የማይንቀሳቀስባት እና እያንዳንዱ ነዋሪ ፈረስን ለመጓጓዣነት የሚጠቀምበት ደሴት የሚገኘው በአሜሪካ ሚቺጋን ግዛት ውስጥ ነው፡፡
የ600 ሰዎች መኖርያ በሆነቸው “ማኪናክ” በተሰኘችው ደሴት ነዋሪዎቹ ለመጓጓዣነት እያንዳንዳቸው ፈረሶችን ይጠቀማሉ፡፡ በአጠቃላይ በደሴቲቱ 600 ፈረሰኞች መኖራቸውም ነው የተነገረው፡፡
እንደ ፎርድ፣ ጄነራል ሞተርስ እና ክራይስለር ያሉ ኩባንያዎች መቀመጫ በሆነችው እና “ሞተር ሲቲ” የሚል ስያሜ በተሰጣት በሚቺጋን ግዛት መኪና ማሽከርከር ክልክል የሆነበት ደሴት መኖሩ ያስገርማል፡፡
ደሴቲቷ የምትገኘው ከሚቺጋን ግዛት በሂሮን ሐይቅ ሰሜናዊ የባሕር ዳርቻ ሲሆን በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት መኪናን በማገድ ፈረስ ብቻ ለመጓጓዣነት ጥቅም ላይ ያዋለች ውብ ደሴት ናት ።
ማኪናክ ደሴት 3 ነጥብ 8 ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋት ላይ ያረፈች ሲሆን 600 ነዋሪዎችን ብቻ በውስጧ ይዛለች፡፡
ፈረስ እንደ ንጉሥ የሚታይባት ደሴቷ የሞተር ተሸከርካሪ የማይፈቀድባት ብቸኛዋ የአሜሪካ ደሴትም ነች፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ የሞተር ተሸርካሪዎች የታገዱት በ1898 በነበሩ የደሴቲቱ ባለስልጣናት አማካኝነት ነው፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የአካባቢው ነዋሪዎች ከሞተር ነጻ የሆነ ጸጥታ የሰፈነበት ሕይወት መምራት ጀምረዋል።
የደሴቲቱ ዋነኛ መጓጓዣ ፈረስ ቢሆንም ብስክሌትም በስፋት ጥቅም ላይ እንደሚውል ቢቢሲ አስነብቧል፡፡