የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 27ኛ መደበኛ ስብሰባው የእንስሳት ጤና እና ደህንነት ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል።
በምክር ቤቱ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ፣ ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ በቋሚ ኮሚቴው የተዘጋጀውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን፤ በምክር ቤቱ አባላት ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በሀገሪቱ እየተንሰራፋ የመጣውን ከሰው ወደ እንስሳ እና ከእንስሳ ወደ ሰው ተላለፊ የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን ያካተተ አዋጅ እንደሆነ በውሳኔ ሀሳቡ ተመላክቷል፡፡
ወደ ሃገር የሚገቡትንም ሆነ ከሃገር የሚወጡትን እንስሳት እና የእንስሳት ምርት የዓለም አቀፉን የእንስሳት ጤና ድርጅት አሰራርና ሕግ በተከተለ መልኩ እንዲሆን የሚያደርግና ዘርፉ ለሃገሪቱ ሊያበረክት የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያጎለብት እንደሆነም በቋሚ ኮሚቴው በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ተብራርቷል፡፡
በእንስሳት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች በበቂ እውቀትና ክህሎት ተጠያቂነትን በተላበሰ ሁኔታ እንዲንቀሳቀሱ ሥርዓት የሚያስቀምጥ፤ ወቅቱን የጠበቀ ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን የዳሰሰ የሕግ ማዕቀፍ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው፣ ረቂቅ አዋጁ በዝርዝርና በጥልቀት ታይቶ የተዘጋጀ መሆኑንና በእንስሳት ዘርፍ የሚስተዋለውን ችግር በመቅረፍ ኢትዮጵያ በዘርፉ የምታገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላቅ ወዳለ ደረጃ እንደሚያሻግር ተናግረዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኋላ አዋጅ ቁጥር 1376/2017 ሆኖ በሙሉ ድምጽ መፅደቁን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡