የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በትውልድ ቅብብሎሽ የተገነባ ተቋም መሆኑ ተገልጿል፡፡
116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ቀን እየተከበረ ነው። እለቱን በማስመልከት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ባለፉት 116 አመታት ያለፈባቸውን ሁነቶች የሚያሳይ አውደ ርዕይም ተከፍቷል።
በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር እንደተናገሩት፣ የፌዴራል ፖሊስ በትውልድ ቅብብሎሽ የተገነባ ተቋም መሆኑን አውስተዋል፡፡
ተቋሙ በአመለካቱ የጎለበተ እና በአቅሙ የዳበረ የፌዴራል ፖሊስ አባላትን ማፍራት መቻሉን የገለጹት አፈ ጉባኤው፣ የኢትዮጵያ ብሄር፣ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የተወከሉበት ተቋም በመሆኑ ፌዴሬሽኑ እውቅና ይሰጠዋልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው፣ ተቋሙ የሀገር ብሎም የቀጠናውን ሰላም በማስበከር እየተወጣ ያለውን ኃላፊነት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ፌዴራል ፓሊስ ትልቅ ተቋም ነው፣ከምስረታው ጀምሮ ሰላም እንዲሰፍን እና ወንጀል እንዲቀንስ የራሱን አስተዋፅዖ ሲያደርግ መቆየቱንም ገልጸዋል።
ተቋሙ ያከናወነው ሪፎርም ተምሳሌት መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ፣ በቴክኖሎጂም እየላቀ መሆኑን ተናግረዋል።
ትላልቅ ምርመራዎችን በራስ አቅም ማከናወን የሚያስችል አቅም መፍጠሩን እና ዘመናዊ ትጥቆችን በማደራጀት አገልግሎት ላይ ማዋል መቻሉንም ጠቁመዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ተቋሙን የተመለከቱ የተለያዩ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።
በሀብታሙ ሙለታ