ያልተቀየረ ኢኮኖሚ የጸና ሀገር ሊያቆም አይችልም-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ያልተቀየረ ኢኮኖሚ የጸና ሀገር ሊያቆም አይችልም-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ሚያዝያ 25/2017 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) 3ኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ መርቀው ከፍተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመርሐግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መቀየር የግድ መሆኑን እና ያልተቀየረ ኢኮኖሚ የጸና ሀገር ሊያቆም እንደማይችል ተናግረዋል፡፡

ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ ኢንዱስትሪውን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምራች ኢንዱስትሪው በራሱ ማደግ ብቻ ሳይሆን ለአምስቱ የኢኮኖሚ ምሶሶዎች ድልድይ ሆኖ ማዘመንና መቀየር እንዲችል ታስቦ የተዘጋጀ የ10 ዓመት የብልጽግና እቅድ መሆኑን አውስተዋል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪው ለግብርው ዘርፍ ድልድይ ሆኖ በዘርፉ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡

በሀገር ውስጥ በርካታ ማሽኖችን መገጣጠም እና ማምረት በመቻሉ እስከ 1 ቢሊዮን ለኢምፖርት ይወጣ የነበረን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉን አስታውሰዋል፡፡

ቡና ላለፉት ረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ ኤክስፖርት ከፍተኛውን ድርሻ ሲጫወት መቆየቱን በማስታወስ ዘንድሮ 400 ሺ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል፡፡

ይህም ለውጡ ሲጀመር ከነበረበት 700 ሚሊየን ዶላር ወደ 3 እጥፍ ያደገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በሌላ በኩል የማዕድን ዘርፉ አንዱ ምሶሶ እንደመሆኑ የማእድን ሀብትን ለመጠቀም አምራች ኢንዱስትሪው ጉልህ ሚና አለው ብለዋል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪው ባለፉት 2 ኤክስፖዎች ኢትዮጵያ ወርቅ ማምረት የምትችልባቸውን ማሽኖች ማምረት በመቻሉ እና በመደገፉ ወርቅ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከቡና በልጦ ትልቅ የኤክስፖርት ድርሻ መውሰዱን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት 10 ወራት ወደ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ወርቅ ኤክስፖርት ተደርጓልም ነው ያሉት፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review