የኢትዮጵያ ፖሊስ በሀገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ዘርፈ ብዙ በሆነ መልኩ አቅሙን ማሳደግ እንደቻለ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡
116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ብሔራዊ የምሥረታ ቀን የማጠቃለያ መርሐ-ግብር ዛሬ በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል፡፡
በዓሉ “ያደገ ፖሊስ እየተለወጠ ላለ ሀገር” በሚል መሪ ሃሳብ ባለፉት ቀናት በተለያዩ ፕሮግራሞች ሲከበር ቆይቷል፡፡
በዛሬው የማጠቃለያ በዓል ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የጦር ሀይሎች አዛዥ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ከፍተኛ የፖሊስ ተቋማት አመራሮች፣ ተጋባዥ እንግዶች፣ እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አዛዦች፤ አመራሮችና ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
በመርሐ-ግብሩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል የኢትዮጵያ ፖሊስ ከተመሰረተ ረዥም እድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም በተደራጀ መልኩ በአዋጅ የተቋቋመው ሚያዝያ 29 ቀን በ1901 ዓ.ም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በወቅቱ የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት የማስከበር ሀላፊነት በመውሰድ “የአራዳ ዘበኛ” በሚል ስያሜ ይጠራ እንደነበር ያስታወሱት ከሚሸነሩ፣ እንደየ ስርዓተ መንግስቱ የተለያየ ፖሊሲያዊ አገልግሎት ሲሰጥ ብዙ የሚያስመሰግኑና የሚያስወቅሱ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አንስተዋል፡፡
በ2010 ዓ.ም በሀገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ መንግስት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ባለፉት 7 የለውጥ ዓመታት በተቋሙ ሁለንተናዊ ለውጥ በማምጣት ዘርፈ ብዙ በሆነ መልኩ የፖሊስን አቅም ማሳደግ እንደተቻለ ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት፡፡
ፖሊስ ወንጀልን ለመከላከል ማህበረሰቡን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳተፍ እና የወንጀል መከላከል መርህን በመከተል እንደ ሀገር የሚሰጡትን ግዳጆች ለመወጣት የሚያስችል በሰው ሀይል አቅም እና በዘመናዊ ትጥቅ መደራጀቱንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
ከለውጡ በኋላ ተቋሙ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት መረጃና ማስረጃን መሰረት ያደረገ የወንጀል ምርምራ መርህን በመከተል በተለይ ስራዎች በሰለጠነ የሰው ሀይል እና በዘመናዊ የፎረንሲክ ምርመራ በመታገዝ ሰብአዊነትን ባከበረ መልኩ ትላልቅ ምርመራዎችን የማካሄድ አቅም መፍጠር እንደተቻለም ኮሚሽነር ደመላሽ ገልጸዋል፡፡
በአስማረ መኮንን