ፓርቲዎች ለአገር ጥቅም መሳካት የተቀናጀ ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል-የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

You are currently viewing ፓርቲዎች ለአገር ጥቅም መሳካት የተቀናጀ ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል-የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

AMN-ሚያዝያ 26 /2017 ዓ.ም

ፓርቲዎች ለአገር ጥቅም መሳካት የተቀናጀ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ “ጠንካራ ፓርቲ፣ጠንካራ መንግሥት፣ ጠንካራ አገር” በሚል መሪ ሃሳብ ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በዓድዋ ድል መታሰቢያ አካሂዷል።

በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራር አባላት፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ፓርቲዎች በተለያዩ ጊዜያት የዜጎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት እንዲጎላ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ዘልቀዋል።

ፓርቲዎች የእኩልነት፣ የፍትህና የአንድነት እሴቶች ተጠብቀው ዘላቂ እድገት እንዲመጣ የማይተካ ሚና መጫወታቸውን ገልጸው፤ ይሄ ሚና ቀጣይነት እንዲኖረው በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ እየተሳተፈና በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከፍ ያለ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቅሰዋል::

ፓርቲው በሁለተኛ መደበኛ ጉባኤው ለአገር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ይበልጥ የሚያሳድግበትን ውሳኔዎች እንደሚያሳልፍ እምነቴ የጸና ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ ሊቀ መንበር አብዱልቃድር አደም (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ፓርቲው ከምስረታው ጀምሮ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ሰላማዊ የፖለቲካ ባህል እንዲገነባ የድርሻውን እየተወጣ ነው።

በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ልዩነት እንደሚፈታ የገለጹት ሊቀ መንበሩ፤ ለዚህም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለአብነትም ፓርቲው በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን እየተሳፈ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንኑ ሚና አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።

ጠንካራ ፓርቲ ጠንካራ ሀገር ለመፍጠር ትልቅ ሚና አለው ያሉት ሊቀ መንበሩ፤ ፓርቲው ራሱን በማጠናከር የአገር መንግሥት ግንባታ ስራው እንዲሳካ ሚናውን ይበልጥ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ በበኩላቸው፤ ብልጽግና ፓርቲ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲያብብ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አንስተዋል።

ፓርቲዎች በአገራዊ ጉዳይ ላይ በጋራ የሚሰሩበት አውድ መፈጠሩን ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ ጠንካራ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን እውን ለማድረግ ፓርቲው ከሁሉም አካላት ጋር ትብብሩን ለማጠናከር ቁርጠኛ ነው ብለዋል።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀ -መንበር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዓድዋ ላይ የውጭ ወራሪን ድል የነሳነውና የታላቁ ህዳሴ ግድብን ያሳካነው አንድ ስለሆንን ነው ብለዋል።

በጋራ ከሰራን የትኛውንም ችግር መሻገር እንችላለን፤ በቅንጅት በመሥራት አገራዊ ሕልማችንን ለማሳካት መረባረብ ከኛ ይጠበቃል ሲሉም ተናግረዋል።

የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው ለዘላቂ ሠላም ግንባታ የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ለሌሎች ፓርቲዎችም አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል።

የእናት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ሰይፈስላሴ አያሌው (ዶ/ር) የአለችንን አንድ ሀገር ለማጽናት ሁላችንም በኃላፊነት ተባብረን ልንሰራ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ፓርቲው በሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው አብዱልቃድር አደምን (ዶ/ር) በድጋሚ ሊቀ መንበር አድርጎ የመረጠ ሲሆን፤ የብሄራዊ ምክር ቤት አባላትንም መርጧል።

ፓርቲው ቋሚና ተጠባባቂ የኦዲት እና ምርመራ ኮሚሽን አባላት ምርጫም ያካሄደ ሲሆን፤ የተሻሻለውን የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብም ጸድቋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review