ሁለት መቶ ጊዜ አደገኛ እባቦች እንዲነድፉት ያደረገው ተመራማሪ

You are currently viewing ሁለት መቶ ጊዜ አደገኛ እባቦች እንዲነድፉት ያደረገው ተመራማሪ

AMN – ሚያዚያ 27/2017 ዓ.ም

ቲም ፍሪድ የተባለ በግሉ የሚንቀሳቀስ አንድ ተመራማሪ በየዓመቱ 140 ሺህ ሰዎችን ለሞት እንዲሁም 420 ሺህ ሰዎችን ለአካል ጉዳት ለሚያጋልጠው የእባብ ንድፊያ መፍትሄ የሚሆን ወደር የለሽ ፀረ-መርዝ በደሙ ውስጥ ለመፍጠር በርካታ ጊዜያትን ራሱን ለእባብ መርዝ አጋልጧል።

ኮማ ውስጥ እንዲገባ ያደረጉትን ጨምሮ ለ18 ዓመታት ከ200 በላይ የእባብ ንክሻዎችን በገዛ ፈቃዱ ያስተናገደው እና ራሱን ከ850 በላይ የእባብ መርዝ መርፌዎችን የወጋው ቲም ፍሪድ አላማው በዚህ ዙሪያ ሰፊ ህክምና ባለመኖሩ ምክንያት በአለም አቀፍ ደረጃ የሚታየውን ከፍተኛ ሞት እና የአካል ጉዳተኝነትን ለመቀነስ አለም አቀፍ ፀረ-መርዝ ለመፍጠር እንደሆነ ተናግሯል።

የቲም ፍሪድ ልዩ ፀረ እንግዳ አካላት (Antibodies) ጃኮብ ግላንቪል የተባለን ዶክተር እና የባዮቴክ ኩባንያቸው ሴንቲቫክስን ትኩረትን በመሳቡ የእርሱን ደም በመጠቀም እጅግ አስደናቂ የሆነ ፀረ-መርዝ ኮክቴል ፈጥረዋል።

በዚህም አዲስ ህክምና ከቲም በሽታ የመከላከል ስርዓት 2 ፀረ እንግዳ አካላትን እና መርዝን የሚያጠፋ ትንሽ ሞለኪውልን በማጣመር እንስሳት ላይ የአደገኛ እባቦች ንክሻ ሙከራ አድርገዋል። ከ19 ሙከራዎች ውስጥም በ13ቱ ሙሉ ጥበቃ፥ በተቀሩት 6 ላይ ደግሞ ከፊል ጥበቃ ማድረግ መቻሉን ሜትሮ ዘግቧል።

አሁን ያለው ጥናት ባላደጉ እባቦች ላይ ያተኮረ ቢሆንም ቲም የትላልቅ አደገኛ እባቦችን መርዝ የመከላከል አቅምን መገንባቱ ተመራማሪዎች በሂደት ሁሉንም የእባብ ዓይነቶች የሚሸፍን ሁለንተናዊ ሕክምናን ማዳበር እንደሚችሉ ተስፋ ሰጥቷቸዋል። በሚቀጥሉት 10 እና 15 ዓመታት ውስጥም ቲም ፍሪድ አስተዋፅዖ የአለም አቀፍ የእባብ ንክሻ ህክምናን የመቀየር አቅም አለው ብለው እንደሚያምኑ ዘገባው አመላክቷል።

በሊያት ካሳሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review