የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢትዮጵያ የማምረት አቅም እና ብሩህ ተስፋ እንዳላት የሚያሳይ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀሥላሴ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የሚከናወነውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 2017 ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሚያዚያ 25 እስከ 29 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆየውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 2017 በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከ288 በላይ አምራቾች እየተሳተፉበት ነው፡፡
ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀሥላሴ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ ፍላጎት ምርታማነትን በመጨመር ጥቅል ሀገራዊ እድገትን ማሻሻል መሆኑን ገልጸዋል።
በኤክስፖው የቀረቡት ከቆዳ የተሰሩ የተለያዩ ምርቶች በዓለም አቀፍ የጥራት መመዘኛ መስፈርት ደረጃቸውን ያሟሉ መሆናቸውን ተመልክቻለሁ ብለዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን ማምረት ከማስቻሉም በላይ የኢትዮጵያን የገበያ መዳረሻ የሚያሰፋ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም በማሳደግ የሥራ እድል የሚፈጥርና ነገ የተሻለ ለማምረት መሰረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።
ማምረት የአንድ ሀገር እድገት መሰረት መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ በማምረት ላይ የተሰማሩ ሀገራት ከፍ ያለ እድገት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በኤክስፖው የታየው መነቃቃት የማምረት አቅማችንን ያሳድጋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ምርቶቹ ኢትዮጵያ የማምረት አቅም እንዳላት እና የነገ ተስፋ የሚያሳይ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢትዮጵያ የማምረት አቅም እና ብሩህ ተስፋ እንዳላት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።