
AMN – ሚያዚያ 30/2017 ዓ.ም
“የአዳም ፍጥረት”ን የሚያሳየውን ሥዕል ጨምሮ በማይክል አንጄሎ ሥዕሎች ባጌጠው የሲስቲን ቻፕል ጣሪያ ስር አንድ መቶ ሠላሳ ሦስት ካርዲናሎች ዛሬ ሐሙስ ዕለት ሁለተኛውን የምርጫ ድምፅ ለመስጠት እንደገና ይሰበሰባሉ።
ኤፕሪል 21 ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉትን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስን ለመተካት እጩ ጳጳሳት የካርዲናሎችን ሁለት ሶስተኛውን ድምፅ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።
ትናንት ረቡዕ የተካሄደው የመጀመሪያው ድምጽ አሰጣጥ አለመሳካቱን እና ቀጣይ ምርጫ መኖሩን በሚያመላክት መልኩ በፀሎት ቤቱ የጭስ ማውጫ ጥቁር ጭስ በመልቀቅ ተጠናቋል።
ከጉባኤው የመጀመሪያ ቀን መጠናቀቅ በኋላ ካርዲናሎቹ የቫቲካን የእንግዳ ማረፊያዎች ወደሆነውና ምርጫው እስኪጠናቀቅ ወደሚቆዩበት ወደ ሳንታ ማርታ ገብተዋል።
ዛሬ ሐሙስ ጠዋት የሙሉ ቀን ምርጫ ለማካሄድ ወደ ሲስቲን ቻፕል ከመሄዳቸው በፊት በፖውሎን ቻፕል የጋራ ፀሎት ያደርጋሉ።
በምርጫው 2ኛ ቀን በታቀዱ አራት ዙር ምርጫዎች ሁለት የድምጽ መስጫ ኮሮጆዎች ማቃጠል የሚኖር ሲሆን ነጭ ወይም ጥቁር ጭስ ይሆናል የሚለውም በውጤቱ መሰረት የሚጠበቅ ይሆናል።
የምርጫ ሂደቱ እጩ ጳጳሳት ሁለት ሦስተኛ ድምጽ እስኪያገኙ ድረስ ለቀናት ሊራዘም እንደሚችልም ኤ ቢ ሲ ኒውስ ዘግቧል።
በሊያት ካሳሁን