
AMN – ግንቦት 6/2017 ዓ.ም
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጤሞቴዎስ ከጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱልቃድር ሁሴን ኦማር ጋር ተወያይተዋል፡፡
ሁለቱ ሚኒስትሮች የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚያስችሉ የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
ዶ/ር ጌዲዮን በቅርቡ የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አብዱልቃድር ሁሴን ኦማር የመጀመሪያ ኦፊሴላዊ ጉብኝታችው በኢትዮጵያ ማድረጋችው የሁለቱን አገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ጋር ያላት ግንኙነት በጉርብትና ብቻ የታጠረ ሳይሆን በፈርጀ-ብዙ ዘርፎች የተሳሰረና ስትራቴጂካዊ ዕይታ ያለው ግንኙነት መሆኑን አስታውቀዋል።

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያና በጁቡቲ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በቀጣናዊ ትስስር፣ እንዲሁም በዜጎች ጉዳይ በቅርብ እየተመካከሩ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ሁለቱ ሚኒስትሮች በጅቡቲ ከሚገኙ ኢትጵያውያን ዜጎች ጋር በተያያዘ እንዲሁም በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ትራንስፖርት ኮሪዶር ከማሳለጥ አኳያ የዲኪል ጋላፊ መንገድ ስራ በሚፋጠንበት አግባብ ዙሪያ መክረዋል።

የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱልቃድር ሁሴን ኦማር በበኩላችው የኢትዮጵያና የጅቡቲ ግንኙነት በባህል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በንግድና ኢኮኖሚ ዘርፍ ጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ተቀራርቦ የመስራት ፍላጎት እንዳላችው ገልጸዋል።
ሁለቱ ሚኒስትሮች ኢጋድን ማጠናከር ላይም ተባብሮ ለመስራት መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።