AMN- ግንቦት 10/2017 ዓ.ም
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም በነገው ዕለት ወደ ፑቲን ስልክ እንደሚመቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል።
ትራምፕ የስልክ ውይይቱ “በዩክሬን ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም” ሁነኛ መፍትሄ እንደሚያስገኝ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ ‘ትሩዝ ሶሻል’ በተሰኘው የማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት፣ “ዕለቱ ፈጽሞ መጀመር ያልነበረበት አስከፊው ጦርነት የሚያበቃበት ፍሬያማ ቀን እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
ትራምፕ በቀጣይም ጦርነቱን ለማስቆም ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ እንዲሁም ከተወሰኑ የኔቶ ጥምረት አባል ሀገራት መሪዎች ጋር እንደሚመክሩ አስታውቀዋል።
ሩሲያ እና ዩክሬን ወደ አስከፊው ጦርነት ከገቡ ከሦስት ዓመታት በኋላ ከትናንት በስቲያ ለመጀመሪያ ጊዜ በቱርክዬ ኢስታንቡል ባካሄዱት የሰላም ድርድር፣ የጦር አስረኞችን ከመለዋወጥ ባለፈ ለዘላቂ ሰላም ተስፋ የሚፈነጥቅ አንዳች መግባባት ሳያሳዩ መለያየታቸው ይታወሳል።
ትራምፕ ከሰላም ድርድሩ በኋላ “እኔ ከፑቲን ጋር እስካልተገናኘሁ ድረስ ጦርነቱ የሚቆምበት ሁነኛ መፍትሔ ጠብ አይልም” ሲሉ መናገራቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።