የብራዚል ግብርና የምግብ ዋስትናን ከፍ ለማድረግ ልምድ የሚወሰድበት መሆኑ ተገለጸ

AMN- ግንቦት 13/2017 ዓ.ም

የብራዚል ግብርና የምግብ ዋስትናን ከፍ ለማድረግ ልምድ የሚወሰድበት ዘርፍ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብራዚል ግብርና ዘርፈ ብዙ ውጤት የሚገኝበት፣ በዓለም እጅግ ቀልጣፋ እና ዘመናዊ ከሚባሉት አንዱ እንዲሆን ያስቻሉ ተቋማትን አስደናቂ የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተናል ብለዋል፡፡

ከተመሰረተ 25 ዓመታት ያስቆጠረው ‎የብራዚል ብሔራዊ አቅርቦት ኩባንያም (Conab)፣ በብራዚል የግብርና ፖሊሲ ውስጥ ወሳኝ ሚና ይዞ ከምርት እስከ ገበያ ያለውን ሰንሰለት በጥናት አስደግፎ በመከታተል ውጤታማ የአቅርቦት አስተዳደር እንደሚተገብርም ጠቁመዋል፡፡

ሌላው በጉብኝቱ የተመለከቱት የግብርና ምርምር ኮርፖሬሽን (Embrapa) የተሰኘው መንግስታዊ ተቋም፤ ሀገሪቱን በግብርና ዘርፍ ወደ ኃያልነት ያሸጋገረ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ አፈርን አክሞ ምርታማነትን መጨመር ላይ፣ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የሰብል ዝርያዎችን ማዘጋጀትና ዘላቂ የግጦሽ አያያዝን እንደሚያሻሽልም አመላክተዋል፡፡

አርሶ አደሩ በፈጠራና ቴክኖሎጂ የተደገፉ ስራዎችን እንዲሰራ በማድረግ የሀገር ምልክት ሆኖ እንዳገኙትም አስታውቀዋል፡፡

‎ከ1.5 ሚሊየን በላይ ሰዎችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ በተለያዩ የስራ መስኮች ተጠቃሚ የሚያደርግ የኅብረት ስራ ማህበርን ተሞክሮ መመልከታቸውንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review