የፕሪቶሪያ የሰላም ንግግር ዋና ተደራዳሪዎች የነበሩት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና አቶ ጌታቸው ረዳ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በነበራቸው ቆይታ ጦርነት ያስከተለውን ጥፋት መቀነስ ይቻል እንደነበር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ግጭቱ በሄደበት ርቀት መሄድ አልነበረበትም ያሉት አቶ ጌታቸው ይህንንም ለማስቀረት የተለያዩ መድረኮች ተካሄደው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በጋራ ውይይቶቹ መተማመን ቢኖር ኖሮ ግጭቱን ማስቀረት ይቻል ነበርም ብለዋል፡፡
ከቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች መካከል በተለይም የሰራዊት አመራሮች የበለጠ ለድርድር ፍላጎት እንደነበራቸው አስታውሰዋል፡፡
ከፕሪቶሪያው ስምምነት አስቀድሞ በተደረጉ ውይይቶች የተኩስ አቁም ዕድል ቢፈጠር ብዙ ሰው ማዳን ይቻል እንደነበርም ነው ያወሱት፡፡
ባለፉት ጊዜያት ግጭቶች በመካረራቸው ምክንያት ሰዎች ዋጋ በመክፈላቸው ማዘናቸውንም ነው አቶ ጌታቸው የተናገሩት፡፡ ከዚህ የበለጠ አደጋ ሳይፈጠር የፕሪቶሪያው ስምምነት መከናወኑ መልካም እድል መሆኑን አንስተዋል፡፡
ስምምነቱ እንዳይፈጸም የተለያዩ አካላት እንቅፋት ሆነው እንደነበር እና እስካሁንም ድረስ መፈረሙን በመቃወም የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ አካላት መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
በድርድሩ ወቅት ወደ ማዕከል ሪፖርት የሚያደርጉ የስነምግባር ችግር የነበረባቸው እና የራሳቸውን ፍላጎት ለማስረጽ የሞከሩ አካላት እንደነበሩ በማስታወስ ችግሩን በህገመንግስታዊ መንገድ ለመፍታት መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል፡፡ በድርድሩ ላይ ባለመሳተፋቸው ቅር ያላቸው አካላት እንደነበሩም አስታውሰዋል፡፡
የፕሪቶሪያ ስምምነት አካል የሆነው ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው የመመለስ ስራ አለመሳካቱ እንዲሁም ሰራዊቱ ወደ ሰላማዊ ህይወት አለመመለሱ እንደሚያሳዝናቸው ገልጸዋል፡፡
አሁንም ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ስራ አጀንዳቸው ያልሆኑ ሰዎች እየታዩ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረው አስተዳደር ይህንን ለመፈጸም በቂ ፍጥነት አልነበረውም ያሉት አቶ ጌታቸው መፈጸም የነበረባቸውን ተግባራት መፈጸም የሚያስችል በቂ ፍጥነት አለመያዛችን ትክክል አልነበረም ብለዋል፡፡
ተፈናቃዮችን ለመመለስ የፌዴራል መንግስት ብዙ ስራዎችን ቢሰራም አስተዳደሩ የፌደራል መንግስትን በመውቀስ ነበር ጊዜውን ያጠፋው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የፕሪቶሪያ ስምምነት የትግራይን ህዝብ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ እንዲፈጸም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡