የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ አካል ዳርቻ አወሳሰን፣ ልማትና እንክብካቤ ረቂቅ አዋጅን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
ምክር ቤቱ 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 31ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ አካሂዷል።
በስብሰባው የውሃ አካል ዳርቻ አወሳሰን ልማትና እና እንክብካቤ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።
በምክር ቤቱ የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አወቀ አምዛዬ(ዶ/ር) አዋጁን በተመለከተ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል።
ምክትል ሰብሳቢው እንዳሉት አዋጁ የውሃ አካላት ዳርቻ ርቀትን ለመወሰን፣ የውሃ አካላትን ከብክነት መጠበቅና ለሀገር ጥቅም በአግባቡ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ማድረግ ላይ ያተኮረ ነው።
ከአረንጓዴ አሻራ፣ ገበታ ለትውልድ እና መሰል መርሃ ግብሮች የሚጣጣም ህግ ማውጣት ወሳኝ እርምጃ በመሆኑ አዋጁ መውጣቱን አብራርተዋል።
የውሃ አካላትን የማልማት እና የመንከባከብ ስራው ውጤታማ እንዲሆን አዋጁ አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወትም አስረድተዋል።
አዋጁ የውሃ አካላት ጥበቃና እንክብካቤን በማሻሻል በርካታ ውጤቶችን ይዞ የሚመጣ ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።
የውሃ አካላት ዳርቻ ወሰን እንዲሁም በውሃ አካላት ብክለት የህግ ጥሰቶች ሰፈጸሙ እርምጃ የሚወሰድበትን አግባብ መደንገጉንም አብራርተዋል።
ነባር ሆኑ ወደ ስራ የሚገቡ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች የሚለቁት ፍሳሽ በውሃ አካላት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ትኩረት መስጠቱንም አስረድተዋል።
ምክር ቤቱ በአዋጁ ዙሪያ የቀረበለት ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።