የፖለቲካ ስብራቶችን ለማቃናትና የወል ትርክቶችን ለመገንባት በሚደረገዉ ጥረት ዉስጥ የሚዲያ ባለሙያዎች የበኩላቸዉን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ

You are currently viewing የፖለቲካ ስብራቶችን ለማቃናትና የወል ትርክቶችን ለመገንባት በሚደረገዉ ጥረት ዉስጥ የሚዲያ ባለሙያዎች የበኩላቸዉን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ

AMN – ግንቦት 14/2017 ዓ.ም

ከአሁን ቀደም የነበሩ የፖለቲካ ስብራቶችን ለማቃናትና አሰባሳቢ ትርክቶችን ለመገንባት በሚደረገዉ ጥረት ዉስጥ የሚዲያ ባለሙያዎች የበኩላቸዉን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ባልቻ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ባልቻ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ አመራር እና ሠራተኞች ጋር ተወያይተዋል።

የቀደመው የፖለቲካ ባህል አሸናፊና ተሸናፊ፣ የበላይና የበታች በሚል በብዙ ሴራ የተተበተበ እና ከሀሳብ ይልቅ በጉልበት ላይ የተመሠረተ እንደነበር የገለጹት ሃለፊው ይህንን ስብራት ለማከም የወል ትርክትን መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የወል ትርክት ወንድማማችነትን፣ ፍትሀዊነትን፣ እኩልነትን እና ህብረ ብሔራዊነትን የሚያጠናክር ነዉ ያሉት ኃላፊው፣ ሚዲያዎችም ኢትዮጵያውያንን የሚያሰባስብ ትርክት ከመገንባት አንጻር የበኩላቸዉን ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

አንዳንድ አካላት በማህበራዊ ሚዲያዎች ጭምር የተዛባ መረጃ በማናፈስ ወንድማማችነትንና ህብረ ብሄራዊነትን ለመናድ ጥረት እያደረጉ መሆናቸዉን የጠቆሙት አቶ ሞገስ ባልቻ፣ ለዜጎች ያዘኑና የተቆረቆሩ በመምሰልና ብሶት በመቀስቀስ የግል ፍላጎታቸዉን ለማሳካት እንደሚሞክሩም አዉስተዋል፡፡

መሬት ላይ ያለው እውነት ኢትዮጵያዊያንን ይበልጥ የሚያቀራርብ ነው በማለትም፣ ጥቂት የግል ጥቅም አሳዳጅ ሀይሎች በየወቅቱ ለሚፈጥሩት አፍራሽ አጀንዳ ጆሮ ባለመስጠት ኢትዮጵያን ወደታየላት ከፍታ የማድረስ የጋራ ሀላፊነት እንዳለብን ተገንዝበን ትጋታችንን መቀጠል ይኖርብናል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review