የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ከተማ እና ሀገር አቀፍ ፈተናን በጥሩ ውጤት ለማለፍ በቂ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተፈታኞች ተናገሩ

You are currently viewing የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ከተማ እና ሀገር አቀፍ ፈተናን በጥሩ ውጤት ለማለፍ በቂ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተፈታኞች ተናገሩ

AMN – ግንቦት 15/2017 ዓ.ም

የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ከተማ እና ሀገር አቀፍ ፈተናን በጥሩ ውጤት ለማለፍ በቂ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተፈታኞች ተናግረዋል፡፡

ተማሪ ናትናኤል ካሳይ እና ያብስራ አሜኑ የትንቢተ ኤርሚያስ የመጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ናቸው፡፡ከፊታችን ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ለሚሰጠው የሚኒስትሪ ፈተና ዝግጅት እያደረጉ የሚገኙት ተማሪዎቹ በተሻለ ውጤት ወደ ቀጣዩ ክፍል ለማለፍ ተሰናድተዋል፡፡

እነ ናትናኤልን ጨምሮ የወይራ የመጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም በግላቸው ከማጥናት ባለፈ በትምህርት ቤት ውስጥ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በመተጋገዝ ጭምር እየተዘጋጁ ነው፡፡

መምህራኖቻቸውም የተለያዩ ጥያቄዎችን በማዘጋጀት እያገዟቸው እንደሚገኙ ነው የተናገሩት፡፡

በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ለሚሰጠው ከተማ አቀፍ የ6ኛ ክፍል ፈተናም ተማሪዎች ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡በራሳቸው ጥረት የተሻለ ውጤት ለማምጣት የፈተና መስጫ ቀኑን እየተጠባበቁ መሆኑን ነው ተፈታኞቹ የገለጹት፡፡

እንደ ከተማ ብሎም ትምህርት ቤት ተማሪዎቸቸው ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡና ብቁ እንዲሆኑ የትምህርት ቤቶች እገዛ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በየጊዜው እያደገ የመጣውን የተማሪዎች ውጤት ዘንድሮም ለማሻሻል መምህራንም ሆኑ ትምህርት ቤቶች ለፈተና የሚያዘጋጁ ግብዓቶችን በማሟላት እያገዙ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የሚገኙ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናዎችን በውጤታማነት እንዲያከናውኑ እንዲሁም ተማሪዎች ለነጋቸው በራሳቸው ጥረት የተሻለ መሰረት ጥለው እንዲያልፉ የክፍለ ከተማው ትምህርት ጽ/ቤትም ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡

በክፍለ ከተማው የ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተናን 23 የመንግስት እና 101 የግል ትምህርት ቤቶች 13 ሺህ 598 ተማሪዎችን የሚያስፈትኑ ሲሆን በ8ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ደግሞ 22 የመንግስትና 64 የግል ትምህርት ቤቶች 12 ሺህ 65 ተማሪዎችን ያስፈትናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በፍቃዱ መለሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review