የጣልያን ሴሪ አ ዛሬ ይለይለታል

You are currently viewing የጣልያን ሴሪ አ ዛሬ ይለይለታል

AMN-ግንቦት 15/2017 ዓ.ም

ከሌሎች ሊጎች በተለየ ፉክክሩን እስከመጨረሻ ሳምንት ያቆየው የጣልያን ሴሪ አ የዋንጫ አሸናፊውን ዛሬ ያሳውቃል።

በአንድ ነጥብ ብቻ የተለያዩት ናፖሊ እና ኢንተር ሚላን አጓጊ ጨዋታዎችን ምሽት 3:45 ያደርጋሉ።

ናፖሊ በሜዳው ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ካሊያሪን ሲያስተናግድ ማሸነፍ ዋንጫ ለማንሳት ዋስትና ይሆነዋል።

በ79 ነጥብ ሊጉን የሚመራው ናፖሊ ከካሊያሪ ጋር ባደረጋቸው 10 የመጨረሻ የሴሪ አ ጨዋታዎች ስድስቱን አሸንፏል። ሽንፈት የገጠመው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ናፖሊ 4ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል። በምሽቱ ጨዋታ ድል ከናፖሊ ጋር ከሆነች ለአራተኛ ጊዜ የሴሪ አው ሻምፒዮን ይሆናል።

በዛሬ ጨዋታ በካልያሪ አሰልጣኝ ዳቪድ ኒኮላ በኩል የሚጠበቅ አንድ ወሳኔ አለ። የቡድኑ ዋና ግብ ጠባቂ ኤሊያ ካፕሪል በጥር ወር በውሰት ከናፖሊ የመጣ ነው። በዚህ ጨዋታ እንዴት እምነት ተጥሎበት ይሰለፋል? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል።

ከመሪው በአንድ ነጥብ አንሶ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኢንተር ሚላን ከሜዳው ውጪ በስታዲዮ ጁሴፔ ሲኒጋግሊያ ኮሞን ይገጥማል።

የሲሞኒ ኢንዛጊው ቡድን ባለፈው ሳምንት ወርቃማ ዕድል አባክኗል። ናፖሊ በፓርማ ነጥብ ቢጥልም ኢንተር ላዚዮን ሳያሸንፍ ቀርቷል።

በዛሬ ምሽት ጨዋታም የናፖሊን ነጥብ መጣል ይጠብቃል። ኮሞ በታሪኩ ኢንተር ሚላንን አሸንፎ ባያውቅም የዛሬ ምሽቱ ጨዋታ ቀላል ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም።

ሁለቱም የምሽቱ ጨዋታዎች በተመሳሳይ 3:45 ላይ ይጀምራሉ።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review