በስራ ምክንያት የሚደርስ ጉዳት ከሰራተኛ አልፎ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጫና እንደሚፈጥር ተገለጸ

You are currently viewing በስራ ምክንያት የሚደርስ ጉዳት ከሰራተኛ አልፎ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጫና እንደሚፈጥር ተገለጸ

AMN – ግንቦት 15/2017 ዓ.ም

በስራ ምክንያት የሚደርስ ጉዳት ከሰራተኛ አልፎ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጫና እንደሚፈጥር የአዲስ አበባ ከተማ ስራና ክህሎት ቢሮ ገለጸ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ23ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ22ኛ ጊዜ የአለም የሙያ ደህንነት እና ጤንነት ቀንን የአዲስ አበባ ከተማ ስራና ክህሎት ቢሮ በአውደ ጥናት እያከበረ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ከተማ ስራና ክህሎት ቢሮ የአሰሪና ሰራተኛውን ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበበ ተቀባ እንደገለጹት፤ በሥራ ምክንያት የሚደርስ ጉዳት በሰራተኛ ላይ ብቻ የሚቀር ሳይሆን በድርጅቶች ህልውና ብሎም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚፈጥር ነው።

ለከተማዋ የኢንዱስትሪ ልማት መፍጠንና መስፍፍት ሲታሰብ በቅድሚያ ለስራ ላይ ደህንነት እና ጤንነት መጠበቅ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ያሉት ኃላፊው በዚህም በበጀት ዓመቱ 10 ወራት ውስጥ በህግ ማዕቀፎችና በሞያ ደህንነት ጤንነት አጠባበቅ ላይ ከ17 ሺ ለሚበልጡ ዜጎች ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

ቢሮው ባለፉት ጊዜያት የሙያ ደህንነት እና ጤንነት ላብራቶሪ በማደራጀትና በማጠናከር ለአምራች ኢንዱስትሪዎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በጥናትና ምርምር ስራዎች እንዲሁም የሥራ ሁኔታዎችን ልኬት በመውሰድ ከአለም አቀፍና ሀገራዊ ደረጃ ጋር በማነፃፀር የስራ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ ለማድረግ የሙያ ድጋፍ እየሰጠ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ ባለማወቅ እና በግዴለሽነት በሚፈጠር የጥንቃቄ ጉድለቶች የሙያ ደህንነትን እና ጤንነትን አደጋ ውስጥ የሚከቱ ክስተቶች እንደሚስተዋል አንስተዋል፡፡

በአለም አቀፍና በሃገር አቀፍ ደረጃ የሰራተኞች ቀን መከበሩ ሰራተኞች በስራ ገበታቸው አስፈላጊውን ሙያዊ ጥንቃቄ በማድረግ የሙያ ደህንነትን እና ጤንነትን እንዲጠብቁ ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በራሄል አበበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review