በህዝብ ላይ ላደረስነው ጉዳትና ለፈፀምነው በደል ይቅርታ እንጠይቃለን ሲሉ የቀድሞ የአማራ ክልል ታጣቂዎች ገለጹ

You are currently viewing በህዝብ ላይ ላደረስነው ጉዳትና ለፈፀምነው በደል ይቅርታ እንጠይቃለን ሲሉ የቀድሞ የአማራ ክልል ታጣቂዎች ገለጹ

AMN – ግንቦት 15/2017 ዓ.ም

በተሳሳተ መንገድ በመመራት በህዝብ ላይ ላደረስነው ጉዳትና ለፈፀምነው በደል ይቅርታ እንጠይቃለን ሲሉ የቀድሞ የአማራ ክልል ታጣቂዎች ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል በተሳሳተ መንገድ ወደ ጫካ በመግባት በትጥቅ እንቅስቃሴ ውስጥ የነበሩ በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ትጥቃቸውን ፈትተዋል።

መንግስት፣ ጠመንጃ በመያዝ ጫካ የገቡ ቡድኖች ትጥቃቸውን በመፍታት በክርክርና የሃሳብ የበላይነት ሰላምና ዴሞክራሲን በማፅናት ለጋራ ሀገራዊ እድገት እንስራ የሚል ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ፣ በአማራ ክልል ይንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በመፍታት በይቅርታ ወደ ሰላማዊ ህይወት ተመልሰዋል።

ከተመላሾቹ መካከል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የወገራ ወረዳ ነዋሪ ሲሳይ መኳንንት፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የተሳሰተ መንገድ በመከተል በህዝብና መንግስት ላይ ላደረስነው በደል ይቅርታ እንጠይቃለን ብለዋል።

በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የታየው የልማትና የዴሞክራሲ ተስፋ የሚደገፍ እንጂ ጠመንጃ የሚነሳበት አልነበረም ሲሉም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በተሳሳተ መንገድ ላይ ነበርኩኝ አሁን ትጥቄን ፈትቼ ተመልሻለሁ ያለው የቀድሞ ታጣቂ ሞገስ ብርሃኑ፤ በየትኛውም መመዘኛ ተገቢነትና ተቀባይነት የሌለው እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተን በመቆየታችን ብዙዎቻቸን ተጸጽተናል ብሏል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወቀ አስፈሬ በበኩላቸው፣ በተሳሳተ መንገድ ጥፋት ላይ ተሰማርተው የነበሩ በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች ባለፉት 10 ወራት ትጥቅ በመፍታት ተመልሰዋል ብለዋል።

የመንግስት የሰላም እጆች አሁንም ያልታጠፉ በመሆኑ በጫካ የምትንቀሳቀሱ ወንድሞች የእድሉ ተጠቃሚ መሆን አለባችሁ በማለት ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሰላም የተመለሱ ታጣቂዎች መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review