በአንድ ድንጋይ ብዙ ወፍ

ወጣት ቢተው ዳዊት ሙዚቀኛ ነው። ገጣሚም ነው፡፡ቴአትርንም በተለያዩ መድረኮችና የሥነ ጽሑፍ ምሽት ላይ ይጫወታል፡፡ የኪነጥበብ ዝንባሌ እንዳለው ከተገነዘበ በኋላ በስልጠና ችሎታውን የበለጠ ለማሳደግ ውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የኪነጥበብ የስልጠና ማእከላት ወደ አንዱ ጎራ አለ። በዚያም እንደሱ ለኪነጥበብ ልዩ ፍቅር ያላቸው ወጣቶችን አገኘ፡፡ ቢተውና የኪነጥበብ ስልጠና ለመውሰድ የተገናኙ ወጣቶች ስልጠናው ሲጠናቀቅ ትምህርታቸውን ጨርሰው አልተበተኑም። ትኩረቱን ሙዚቃ፣ ቴአትር ግጥምና ሌሎች የኪነጥበብ ስራዎች ላይ ያደረገ የኪነት ማህበር መሰረቱ፡፡  ስሙንም  ™ሀበሻ ኳየር የኪነ ጥበብ∫ ቡድን አሉት፡፡

ወጣቶቹ አቅማቸውን ለማሳደግ ተጨማሪ ስልጠና ወስደዋል፡፡ ከዚያም በኮልፌ ወረዳ 09 በኪነጥበብ ማህበር ሲደራጁ ወረዳውም ለስራቸው ማቅረቢያ እና ለልምምድ የሚሆን አዳራሽ ፈቀደላቸው፡፡ ስብሰባ ሲኖር፣ የኪነጥበባዊ ምሽቶች በተለያዩ አካባቢዎች ሲዘጋጁ ስራዎቻቸውን ማቅረብ ጀመሩ፡፡ ከተለያዩ ቦታዎችም የኪነጥበብ ስራዎችን እንዲያቀርቡ ግብዣዎች መጡላቸው፡፡ ይህ ደግሞ ተጨማሪ እድል ፈጠረላቸው።

ቢተው እንደሚለው ሁሉም ወጣቶች በጥሩ ስነምግባር የታነጹ፣ በኪነጥበብ ትልቅ ደረጃ መድረስ የሚፈልጉ ናቸው። የሚፈልጉት የኪነጥበብ ስራዎችን መስራት፣ የሀገር ፍቅርን ከፍ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ በኮሪደር ልማት በተሰሩ የህዝብ የመዝናኛ ስፍራዎች የሚቀርቡ የኪነጥበብ ምሽቶች እድልን እየፈጠሩ ነው፡፡

እኛም አንድነትና አብሮነትን መሰረት ያደረጉ ስራዎችን በመስራት፣ እህትማማችነትና አብሮነትን በማጉላት በኪነጥበቡም ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ነው የምንፈልገው፡፡ ስራዎቻችን አንድነትና አብሮነት እንዲሁም የጋራ ትርክርት መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ለምሳሌ  መድረክ ላይ ካቀረብነው አንዱን ልንገርህ ብሎ ቀጠለ፡-

እርስበርስ ጥላቻ መለያየት ቀርቶ

ህዝባችን ይዘምር በአንድነት ወጥቶ

አማራው ኦሮሞው አንድ ቤተሰብ ነው

አፋር ከጉራጌ ትስስር አላቸው፡፡

ሱማሌና ሀረሪ ሰው አክባሪ ናቸው፡፡

ቋንቋችን ቢለያይ ደማችን አንድ ነው፡፡

በሀገሬ ምድር ላይ ተስፋን ሰንቄያለሁ

እናቴም ኢትዮጵያ ሆና አግኝቻታለሁ።

ቢተው እና ጓደኞቹን ጨምሮ ሌሎችም ወጣቶች በኮሪደር ልማት በተሰሩ የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች ሙዚቃ፣ ቴአትርንና ግጥምን ጨምሮ ሌሎች የኪነጥበብ ስራዎችን ያቀርባሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከህዝብ ጋር እንዲገናኙ እድል ፈጥሯል፡፡
ከማህበረሰቡ የሚሰጠን አስተያየትም በጣም ጥሩ ነው፡፡ መንገድ ላይ ስራችንን ስናቀርብ ኪነጥበብን ለማየት ከሚመጡት በተጨማሪ መኪናቸውን አቀሙው ወርደው የሚመለከቱ፣ በማታ ሲዝናኑ በአጋጣሚ አይተው የሚታደሙ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው ይላል ወጣት ቢተው፡፡

ለምሳሌ ጦር ሃይሎች አደባባይ በተዘጋጀው የኪነጥበብ ምሽት ላይ የሙዚቃ ስራ አቅርበን ነበር፡፡ በጣም ብዙ ሰው ነበር የተገኘው፡፡ የሚያልፈው ሰው ሁሉ ቆሞ ሲመለከት ነበር፡፡ ምክንያቱም ኪነጥበብ በተለይ ሙዚቃ ሰውን የመያዝ እና የማዝናናት አቅም አለው፡፡ እኛም ደስተኞች ነበርን፡፡ በየወሩ በመዲናዋ የሚዘጋጀው የኪነጥበብ ምሽት ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ነው ሲልም አክሏል፡፡

ብዙ ጊዜ አንድነት ላይ የተመሰረተ ስራ እንሰራለን፡፡ መነሻችን የሀገር ፍቅር ነው፡፡ ይህን ስሜት ደግሞ በአደባባዮችና በዝግጅቶች ላይ ህዝቡ ስሜቱን ገልጾልናል፡፡ በስራዎቻችንም እየተዝናና ነው፡፡ ሙዚቃ ስናቀርብ ይህን በደንብ አይተነዋል ሲል ያብራራል፡፡

ቢተው አያይዞም የምናቀርባቸው ስራዎች በልማት፣ በመተሳሰብ እና በመተባበር ላይ ነው፡፡ ኪነጥበብ ቅድሚያ ለሰውነትና ለአንድነት ነው፡፡እኛም ሀገር ፍቅር ላይ ነው የምናጠነጥነው። አላማችን እያዝናናን ማስማር፣ እኛም እድሉን ተጠቅመን ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ነው የምንፈልገው በማለት ሃሳቡን ይገልጻል፡፡

ሌላኛው ወጣት ዘላለም እሸቱም ሙዚቀኛ ነው፡፡ የአራዳ ክፍለ ከተማ የኪነት ቡድን መሪም ነው፡፡ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ የኪነጥበብ ስራዎችን በማቅረብ ላይ እንገኛለን፡፡ እኛም ትኩረታችን ሀገራዊ ነገር ላይ ነው፡፡የሙዚቃ ስራዎቻችንም ሆነ አጠቃላይ የኪነጥበብ ስራዎቻችን ሀገር ፍቅር ላይ ፣ አንድነት ላይ፣ ልማት ላይ እና መተሳሰብ ላይ ነው የሚያተኩሩት ይላል፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ በኮሪደር ፕሮጀክት በተሰሩ የመዝናኛ ስፍራዎች እየቀረቡ የሚገኙት የኪነጥበብ ምሽቶች ፋይዳቸው ዘርፈ ብዙ ነው። የኪነጥበብ ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶች አቅማቸውን ለማሳደግ ይረዳቸዋል፡፡ ከብዙ ህዝብ ጋር የሚገናኙበትና በራስ መተማመናቸውን ከፍ የሚያደርጉበት ነው፡፡ በትራንስፖርት የሚሄደው ሰው ዝግጅቱን ያያል፡፡ በእግሩ የሚጓዘው ሰው ቆሞ ይከታተላል፤ ይህ ደግሞ እጅግ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው ሲልም ወጣት ዘለላም ያብራራል፡፡

ለምሳሌ ሙዚቃ አቅሙ ትልቅ ነው፡፡ የሰዎችን ስሜት የመግዛት አቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡ ሰዎች በሙዚቃ የሰሙትን ነገር አይረሱትም፡፡ ስለኢትዮጵያ የተዘፈኑ ዘፈኖችን ብዙ ሰው የሚያስታውሳቸው፣ በስሜት የሚያዜማቸውም ለዚያ ነው። ለዚያም ነው 4ኪሎ ፕላዛ በተዘጋጀው የኪነጥበብ ምሽት ጨምሮ ስለ አንድነት፣ አብሮነት፣ ፍቅርና፣ ሀገራዊ ስሜት ከፍ የሚያደርጉ መልእክቶችን በሙዚቃ እያዋዛን የምናቀርበው፡፡

በኪነጥበብ ምሽቶቹ ላይ የተለያዩ የብሔር ብሔረሰብ ሙዘቃዎችንም እናቀርባለን፡፡ አልባሳቶችም እየተሟሉልን ነው፡፡ ኪነጥበባዊ ስራዎች መልዕክታቸው ሳይሆን አቀራረባቸውም ህብረብሔራዊ ነው በማለት ዘላለም እሸቱ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አጋርቷል፡፡

ወጣት ቢተው በበኩሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኪነጥበብ የተሰጠው ትኩረት ትልቅ ነው፡፡ ድጋፎችም እየተደረጉ ነው። ከዚህ በላይ የቁሳቁስና ሌሎች ድጋፎች ቢደረጉ ደግሞ በሙዚቃና ኪነጠበብ ብዙ ስራ ማከናወን ይቻላል የሚለው ቢተው በሙዚቃ ህዝብን ወደ አንድ ማምጣት ይቻላል፡፡ ለልማት ማነሳሳት ይቻላል። ከተረጅነት ወደ ረጅነት መቀየር ይቻላል፡፡ ስመጥር አርቲስቶችን መፍጠር ይቻላል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በአንጻራዊነት ምቹ ነባራዊ ሁኔታ አለ ሲልም ሃሳቡን ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አጋርቷል፡፡

ለዚህ ደግሞ የሁሉም ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡ እኛም ገና ጀማሪ ነን። ብዙ ስራ ሰርተናል ማለት አንችልም። ትልቅ አቅም ግን አለን፡፡ በየወሩ በአዲስ አበባ በኮሪደር ፕሮጀክት በተሰሩ መዝናኛ ስፍራዎች በሚዘጋጁ ሥነጽሑፍ ምሽቶችና ሌሎችም ዝግጅቶች ሌሎችን ለማዝናናት፣ የጋራ አመለካከትን ለማሳደግ እና ሀገራዊ ፍቅርን ከፍ ለማድረግ እንዲሁም ለእኛ ለሙዚቀኞችና የኪነጥበብ ባለሙያዎች  እድል በመፍጠር ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው፤ ስለዚህ ይህን አቅም ተረድተው ባለድርሻ አካላት ኪነጥበቡን በአቅማቸው ልክ መደገፍ አለባቸው በማለትም አክሏል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ የኪነጥበብ ምሽት ከሚያዘጋጁት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አብዩ ጌታቸው ከዚህ ቀደም ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በሰጡት አስተያየት  ኪነ ጥበብ የወል ትርክትን ለመገንባት፣ የጋራ እውነት እና አረዳድን ለመፍጠር አይነተኛ መሳሪያ ነው፡፡ ይህ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው የኮሪደር ልማት  የፈጠረዉን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም፣ የኮሪደር ልማቱ ትሩፋት በሆኑ የመዝናኛ ቦታዎች መቅረቡም ልዩ ያደርገዋል፡፡

አቶ አብዩ በየወሩ የኪነጥበብ ምሽት በማዘጋጀት ላይ እንገኛለን። የኪነጥበብ ስራዎች ይዘት ደግሞ አንድነት፣ ወንድማማችነት፣ መከባበር እና አብሮነት ላይ መሰረት ያደረገ ነው፡፡የኪነጥበብ ምሽቱ ብዙ አላማዎች አሉት። የመጀመሪያው የጋራ ትርክትን መገንባት ነው፡፡ ሁለተኛው በኮሪደር ልማቱ በተሰሩ መዝናኛ ቦታዎች ላይ ፕሮግራሙን በማቅረብ የልማት ስራዎችን ማስተዋወቅ ነው፡፡ ሶስተኛው ደግሞ ተተኪ የኪነጥበብ ባለሙያ ለማፍራት ይረዳ ዘንድ ወጣቶች ከአንጋፋ አርቲስቶች ልምድ እንዲቀስሙ ማድረግ ነው ብለው ነበር፡፡

የኪነጥበብ መርሃ ግብሮቹ የሚካሄዱት በህዝብ መዝናኛ እና መናፈሻ ቦታዎች ነው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ከተጋበዙት እንግዶች በተጨማሪ በእግር የሚጓዙ ሰዎች፣ የሚዝናኑ ሰዎችም እንዲታደሙ እድል ፈጥሯል በማለት የወጣት ዘላለም እና ቢተውን ሃሳብ የሚደገፍ አስተያየት ሰጥተዋል ፡፡

የኪነጥበብ መርሃ ግብሩን ከሚታደሙ ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ መስፍን ካሳም እንደዚህ አይነት ፕሮግራሞች መኖራቸው የሚበረታታ ነው፡፡ እኔ ማታ ማታ በእግር መጓዝ እወዳለሁ። ማረፍ ስፈልግ ደግሞ አዳዲስ በተሰሩ የመናፈሻ ቦታዎች ነው፡፡ ይህ የተለመደ ተግባሬን እያከናወንኩ ሳለ ሁለት የኪነጥበብ ምሽቶች አጋጥመውኛል ሲሉ ስለኪነጥበብ ምሽቱ አስተያየታቸውን አጋርተዋል፡፡

ኦዱሪ ዩኢ የተባሉ የዘርፉ ባለሙያ እ.ኤ.አ በ2020 “The role of arts and culture in resilient cities: creativity and placemaking” በሚል በጻፉት መጽሐፍ ላይ እንደጠቀሱት በአንድ ከተማ ሙዚቃን ጨምሮ የሚሰናዳ የኪነጥበብ ምሽት ለአንድ ሀገር ለውጥ ዘርፈ ብዙ ሚና ይጫወታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገቶችን ያፋጥናል። የማህበረሰብ ተሳትፎን ያበረታታል፡፡ የአብሮነት ባህልን እና የከተሜነት እሳቤን ከፍ ያደርጋል፡፡

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review