
AMN- ግንቦት 16/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻን ሊያካሄድ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ገለጸ::
ዘመቻው እድሜያቸው ከዘጠኝ ወር እስከ ከአምስት ዓመት የሆኑ ህጻናት ከግንቦት 18 እስከ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች እና በጤና ተቋማት እንደሚሰጥ ቢሮው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል::
ለዚህም ተግባር በከተማ አስተዳደሩ ያሉ 94 የጤና ጣቢያዎች እና 1 ሺህ 536 ጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች ዝግጁ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮናስ ጫላ በሰጡት ጋዜጣዊ በመግለጫ ተናግረዋል::
የቫይታሚን ኤን ጨምሮ ለምግብ እጥረት የተጋለጡ ህፃናትን መለየት፣ ከተወለዱ ጀምሮ ምንም ክትባት ያልወሰዱ ህፃናትን እንዲሁም በወሊድ ምክንያት የተጎዱ እናቶችን መለየት፣ የክትባት ክትትል ባለማድረግ ለህመም የተጋለጡ ህፃናትን የመለየት ስራ በዘመቻው የሚከናወን መሆኑም በመግለጫው ተመላክቷል::
ዘመቻው የተሳካ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት እና የከተማው ነዋሪ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ ተላልፏል::
በታምሩ ደምሴ