የከተማችን አደጋ የመቋቋም አቅም እንዲጎለብት ጠንክረን እንሰራለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

You are currently viewing የከተማችን አደጋ የመቋቋም አቅም እንዲጎለብት ጠንክረን እንሰራለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

AMN – ግንቦት 17/2017 ዓ.ም

ከንቲባዋ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ዛሬ ማለዳ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ እየተከበረ ያለውን የእሳት እና ድንገተኛ አደጋ ሰራተኞች ቀንን በድምቀት አክብረናል ብለዋል፡፡

እለቱ በእሳት እና ድንገተኛ አደጋን መቆጣጠር ስራ ወቅት መስዋዕት የሆኑ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞቻችንን የምንዘክርበት እና በስራ ላይ ያሉ እሳት ውስጥ ገብተው እሳት የሚያጠፉ ጀግኖቻችንን ደግሞ ክብርና እውቅና የምንሰጥበት ነው ብለዋል።

ከንቲባዋ አክለውም ተቋሙን በሰው ሃይልና በሎጂስቲክ በማደራጀት ዘመናዊ የእሳት አደጋ መከላከል ተቋምን ለመገንባት የጀመርነው ስራ ፍሬ እያፈራ የሚገኝ ሲሆን፣ በኮሪደር ልማት ዘመናዊ መሰረተ ልማት በመዘርጋት አደጋውን ይበልጥ ለመቀነስ በመስራት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

የእሳት አደጋ መከላከል ሰብአዊነት የተሞላበት እና እሳት ውስጥ በመግባት እሳት በማጥፋት ህይወት የሚታደግበት እንዲሁም ንብረት ለማትረፍ የሚሰራ በጎ ስራ ነው ያሉት ከንቲባዋ፣ በከተማችን በጀመርነው የኮሪደር ልማት ስራ እሳትን የምንከላከለው በልማት በመሆኑ 129 የፋየር ሃይድራንቶችን በመዲናችን የተለያዩ አካባቢዎች በመገንባት አደጋውን ለመከላከል ከተማችን ዝግጁ መሆኗን ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል፡፡

የከተማችን አደጋን የመቋቋም አቅም እንዲጎለብት ጠንክረን እንሰራለን ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ እንኳን ለዓለም አቀፉ የእሳት አደጋ ሰራተኞች ቀን አደረሳችሁ ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review