አሜሪካ የገባችዉን የታሪፍ ስምምነት ጥሳለች ስትል ቻይና አስታወቀች

You are currently viewing አሜሪካ የገባችዉን የታሪፍ ስምምነት ጥሳለች ስትል ቻይና አስታወቀች

AMN- ግንቦት 25/2017 ዓ.ም

አስተያየቱ የመጣው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባለፈው ዓርብ “ቻይና ከእኛ ጋር የገባችውን የታሪፍ ስምምነት ሙሉ በሙሉ ጥሳለች ማለታቸውን ተከትሎ ነው፡፡

የታሪፍ ስምምነቱ መጣሱን ተከትሎም፣ ቻይና ጥቅሟን ለማስከበር እና ለመከላከል ስትል ጠንካራ እርምጃ እንደምትወስድ አስታዉቃለች፡፡

የቻይና የንግድ ሚኒስቴር ፣ ዋሽንግተን ባለፈው ወር በጄኔቫ በተካሄደው ውይይት ላይ የተደረሰውን ስምምነት አፍርሳለች ብለዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት አንዳቸው ከሌላው በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የታሪፍ ቅናሽ ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸው የሚታወስ ነው፡፡

የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ባለፈው ጥር ወር በስልክ ያደረጉትን ስምምት አሜሪካ መጣሷን ነዉ የቻይናው የንግድ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ያስታወቁት፡፡

ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸዉ ቻይና “ከእኛ ጋር የገባችውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ጥሳለች” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጉዳዩን አስመልክቶ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም፣ የአሜሪካው የንግድ ተወካይ ጄሚሰን ግሬር ቻይና በስምምነቱ መሰረት ከታሪፍ ውጪ የሆኑ እንቅፋቶችን እያነሳች እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ሃገራት በጄኔቫ ባካሄዱት የንግድ ስምምነት ዩናይትድ ስቴትስ ከቻይና በሚመጡ ሸቀጦች ላይ የጣለችውን ቀረጥ ከ145 በመቶ ወደ 30 በመቶ ዝቅ አድርጋለች።

ቻይና በበኩሏ በአሜሪካ ምርቶች ላይ የጣለችውን የበቀል ታሪፍ ከ125 በመቶ ወደ 10 በመቶ አውርዳለች፡፡

ነገር ግን አሜሪካ የገባችውን ስምምነት በመጣስ የኮምፒዩተር ቺፕ ዲዛይን ሶፍትዌርን ለቻይና ኩባንያዎች መሸጥ አቁማለች ስትል ነዉ ቻይና የከሰሰችዉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በቻይናው ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሁዋዌ የተሰሩ ቺፖችን እንዳትጠቀሙ ስትል ማስጠንቀቂያ መስጠቷና የቻይና ተማሪዎች ቪዛ መሰረዝም አሜሪካ ከጣሰቻቸዉ ስምምነቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ መሆናቸዉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review