ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት የብዝኃነት ማሳያ የአብሮነታችን ምሳሌ መሆናቸውን የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት የብዝኃነት ማሳያ እና የአብሮነት ምሳሌ የሆኑባት ሀገር እንደሆነችም አገልግሎቱ አመላክቷል፡፡
በዓላቱ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ብሔራዊ፣ የቤት ውስጥ ወይም የዐደባባይ ሊሆኑ ይችላሉ፤ መሠረተ ሐሳባቸው ግን ደስታን፣ ተስፋን፣ ብሔራዊነትን መጋራት እና መተጋገዝ ነው ብሏል አገልግሎቱ።
ዛሬ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ የሚገኘዉ የኢድ አል-አድሃ(ዐረፋ) በዓል መረዳዳት፣ መተሳሰብና አንድነት ጎልቶ ከሚንጸባረቅባቸዉ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል አንዱ ነው።
በዚህ በዓል ያለው ለሌለዉ ማዕድ የሚያጋራበት፣ አብሮነትና ወዳጅነት የሚያጠናክርበት መሆኑን አገልግሎቱ አንስቷል፡፡
ብዝኃነትን ጌጥ፣ መረዳዳትንና ማዕድ ማጋራትን ባህል እያደረገ የመጣዉ የለውጡ መንግሥትም እነዚህ በዓላት የብዝኃነት እና የአብሮነት ማሳያ እንዲኾኑ አስፈላጊዉን እንክብካቤ እና ጥበቃ ያደርጋል ብሏል።
አገልግሎቱ አክሎም፣ ዜጎች ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላትን በድምቀት እና በአብሮነት እንዲያከብሩ መንግሥት አበክሮ ይሠራል ብሏል።