በሆስፒታሉ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ታሪኩ ገልዳ እንደገለጹት ሁለት ሰዓታት በፈጀው ቀዶ ህክምና እሳቸውን ጨምሮ ሰባት የህክምና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡
ይህም በሆስፒታሉ የህክምና ታሪክ ከ70 አመት አዛውንት ማህጸን 14 ኪሎ ግራም የሚዝን እጢ በቀዶ ህክምና ሲወጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ብለዋል፡፡
በነገሌ ቦረና ሆስፒታል ደረጃ ከመለስተኛ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ በስተቀር የዚህን ያክል ቀዶ ህክምና ተደርጎ እንደማይታወቅ ገልጸዋል፡፡
ከአዛውንቷ ማህጸን በቀዶ ህክምና የተወገደው እጢ ለ16 አመታት ያክል አብሯቸው እንደኖረ በምርመራ መረጋገጡንም ተናግረዋል።
ዜጎች የጤና ችግር ሲገጥማቸው በባህላዊ መንገድ ለማስወገድ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ወደ ህክምና ተቋም ቢመጡ በአጭር ጊዜ መፍትሄ እንደሚያገኙም መክረዋል፡፡
በምስራቅ ቦረና ዞን ሊበን ወረዳ የቀርሳማሊ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ሀቢባ አሬሮ፤ በሽታው ምግብ ስለከለከላቸው ውሀና ወተት ብቻ በመጠጣት ለዓመታት እንዳሳለፉ ተናግረዋል፡፡
በባህላዊ መድኃኒትና በጤና ተቋማት ህክምና ለመዳን ባደረጉት ክትትል በብዙ ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ማባከናቸውን አስታውሰዋል፡፡
”የጉበት በሽታ ነው” በሚል በየ6 ወሩ ከውስጣቸው በመርፌ ውሀ ይቀዳ እንደነበር የተናገሩት አዛውንቷ ወደ ነገሌ ቦረና ሆስፒታል በመምጣት ባገኙት ህክምና እፎይታ ማግኘታቸውን መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወይዘሮ ሀቢባ፤ ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን በሰብል ልማት የሚተዳደሩ የዘጠኝ ልጆች እናት መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡