በለውጡ ዓመታት በብሀሃነት ውስጥ ኢትዮጵያን ወደ ወደ ብልፅግና የሚያሸጋግሩ ምቹ መደላድል እና አኩሪ ተግባራት መከናወናቸውን የብልፅግና ፓርቲ ዓለም አቀፍና የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ሀላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
”የድህረ እውነት ዘመንን በእውቀትና በእውነት” በሚል መሪ ሃሳብ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን የአመራር ስልጠና በባህርዳር ከተማ እየተሰጠ ይገኛል።
በስልጠናው መድረክ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፥ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያውያንን ይበልጥ እርስ በእርስ የሚያስተሳስሩ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
እነዚህም ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን፣መከባበርንና መተጋገዝን በማጎልበት በብዝሃነት ውስጥ ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና የሚያሸጋገር ምቹ መደላድል እና አኩሪ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።
እንዲሁም የዜጎች የስራ ባህል እንዲጎለብትና በሃገራቸው ሰርተው ሃብት ማፍራት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አመልክተው፤በስኬታማነት እየተገባደደ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና የባሕር በር ጉዳይ አጀንዳ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል።
ለዚህ ውጤት መገኘትም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የጎላ ሚና ማበርከቱን ጠቅሰው፥አሁንም ዘርፉ እውነትን አጉልቶ በማውጣት የጋራ ትርክት የመገንባትና ብሄራዊ ጥቅምን የማስከበር ሚናውን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የዚህ ስልጠና ዓላማም የተገኘውን ድል በሃሳብ የበላይነት አጠናክሮ ለማስቀጠል በእውቀት፣በክህሎትና በአመለካከት የዳበረና የተናበቡ ስራዎችን ለማከናወን ታሳቢ የተደረገ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በአማራ ክልል ፅንፈኛው ቡድን ለክልሉ ሕዝብ ልማት፣እድገትና ብልፅግና የሚጨነቅ አለመሆኑን በተግባር ተረጋግጧል ያሉት ደግሞ በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ ገለፁ።
በተወሰደው የህግ ማስከበር እርምጃ የፅንፈኛውን ቡድን አጥፊ ተግባር በመቀልበስ ሰላምን ከማስፈን ባሻገር የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት የሚያጠናክሩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በፓርቲያችን ኢኒሼቲቮች መሰረት በከተሞች የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የአባይ ተለዋጭ ድልድይና ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ በማጠናቀቅ በተግባር ማሳየት ተችሏል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
እንዲሁም ጎርጎራ ፕሮጀክትና የመንገድ መሰረተ ልማቶች የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ስራዎች እንደሆኑም አንስተዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ለሶሰት ቀናት በሚቆየው ስልጠና በክልሉ ከሚገኙ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የተወጣጡ አመራሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተመልክቷል።