ሀገርን በፅኑ መሰረት ላይ በሚያቆሙ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠር የሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ

You are currently viewing ሀገርን በፅኑ መሰረት ላይ በሚያቆሙ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠር የሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ

AMN ሰኔ 19/2017

በሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያን በፅኑ መሰረት ላይ በሚያቆሙ እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ “ለስኬታማ ሀገራዊ ምክክር የሃይማኖት ምሁራን ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ ከተለያዩ ሃይማኖት ተቋማት ምሁራን ጋር በአዲስ አበባ ውይይት እያደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሀሙድ ድሪር በውይይቱ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር፣ የሃይማኖት ተቋማት ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት መከበር ትልቅ አበርክቶ አላቸው ብለዋል።

ኮሚሽኑ በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተመካክሮ የጋራ መግባባት ለመፍጠር አካታች የውይይት አጀንዳ ልየታ እያጠናቀቀ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ እየመከረች ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፥ የሃይማኖት ተቋማትና ምሁራኑ ለሀገር ጸንቶ መቀጠልና ለዘላቂ ሰላም የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ ምክክሩ ታሪካዊ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት የሀሳብ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በውይይት መፍታት ወሳኝ መሆኑን በዕለት ተዕለት የእምነት አስተምህሮ ውስጥ እያነሱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ይህም የኮሚሽኑን ዓላማ የሚደግፍና ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ በመሆኑ ኮሚሽኑ የሃይማኖት ተቋማት ያላቸውን ሚና በመገንዘብ በምክክር ሂደቱ ቁልፍ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረጉን አመልክተዋል።

የሃይማኖት አባቶች በተከታዮቻቸው ዘንድ ያላቸውን ተሰሚነትና ተቀባይነት በመጠቀም አለመግባባቶች በውይይት ብቻ መፍትሔ እንዲያገኙና የሀገርን ቀጣይነት የሚያረጋግጥ ዘላቂ ሰላም ማምጣት ላይ በጋራ እንሰራለን ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት በአጀንዳ ማሰባሰቡ ሂደት በንቃት መሳተፋቸውን አስታውሰው በቀጣይ በትግራይ ክልል በሚካሄደው የተሳታፊዎች ልየታና አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እስኪፈጠርና ዘላቂ መፍትሔ እስኪመጣ የሃይማኖት ተቋማትና ምሁራኑ ድርብ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

እንደአንድ ባለድርሻ አካል በምክክር ሂደቱ በመከባበር፣ በመደማመጥና ርህራሄ በተሞላበት መንፈስ በመመካከር፤ በሌላ በኩል ሌሎች የምክክሩ ተሳታፊዎች በዚሁ መንፈስ በምክክሩ ሂደት ላይ እንዲሳተፉና ወደ መግባባት እንዲመጡ ምሁራዊና አባታዊ ሚናቸውን እንዲወጡ ነው የጠየቁት።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review