በስራ በመሰማራት ላይ የነበሩ የባለስልጣኑን ኦፊሰሮች ያለፈቃድ ፎቶ በማንሳት በቲክቶክ ያሰራጨው ግለሰብ በፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዲውል ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ግለሰቡ ፎቶ በማንሳት በቲክቶክ ያሰራጨዉ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፋለ ከተማ ወረዳ 04 በስራ ስምሪት ላይ የነበሩ የደንብ ማስከበር አባለትን መሆኑን ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ ተናግረዋል።
ግለሰቡ ያለፈቃዳቸው ፎቶ በማንሳትና ቪዲዮ በመቅረጽ በቲክቶክ በማሰራጨቱ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸዋል።
ግለሰቡ በመደበኛ ስራቸው ላይ የነበሩ ኦፊሰሮችን ተከታትሎ ፎቶ በማንሳትና ቪዲዮ በመቅረጽ ስም ከማጥፋቱም በላይ የስራ እንቅስቃሴዎችን ከህግ አግባብ ውጪ ሲያሰራጭ የነበረ መሆኑ እንደተደረሰበት ተናግረዋል።
ግለሰቡን በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውል በማድረግ ተጨማሪ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑንም ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ጨምረዉ ገልጸዋል።
በወንድማገኝ አሰፋ