የህብረተሰቡ ችግኝ የመትከል ልምዱ እያደገ በመምጣቱ ከከተማ አስተዳደሩ ዕቅድ አንፃር ከፍተኛ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ ገልፀዋል፡፡
የ2017 ክረምት 7ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ ደረጃ ከንቲባ አዳነች አበቤ እና የተለየዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ከቀናት በፊት የማስጀመሪያ መርሐ-ግብር መከናወኑ ይታወሳል፡፡
የማስጀመሪያ መርሐ-ግብሩ የሃይማኖት አባቶች፣ አትሌሎቶች፣ መምህራን እና ተማሪዎች፣ አንዲሁም የጤና ባለሞያዎች እና የተለያዩ የህበረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ አካላት በተገኙበት በከተማ ደረጃ ችግኞች መትከላቸውን እና የነበረው ሁኔታም ልብን የሚያሞቅ ምሳሌ የሚሆን ተግባር እንደነበር አቶ ግርማ ለኤ ኤም ኤን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ለሚከናወኑ ተግባራት ከተማ አስተዳደሩ በበቂ ሁኔታ ችግኝ ማዘጋጀቱንና በዚህ ክረምት እንደ ከተማ 4.2 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል መታቀዱንም አብራርተዋል፡፡
ለዚህም በህብረተሰብ ተሳትፎ 2.4 ሚሊየን ጉድጓድ መዘጋጀቱንና አስፈላጊ ዝግጅት መደረጉን የገለፁት ኃላፊው፣ ህብረተሰቡ ይፋ በሚደረግለት መርሐ-ግብር መሰረት አሻራውን እንዲያስቀምጥ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
አሁን ላይ እንደ ከተማ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከ86 ሚሊየን በላይ ችግኝ በመትከል የከተማዋን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ማሳደግ ተችሏል ያሉት ኃላፊው፣ በቀጣይም የከተማዋን የደን ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በወንዝ ዳርቻ ያሉ አካባቢዎች ላይ ትኩረት በመስጠት ለምግብነት የሚውሉ የተክል ዝርያዎችን በመትከል የምግብ ዋስትናችን ለማረጋገጥ ስራዎች ይሰራሉም ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የደን ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ እንደሆነና የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብርን በስኬት ለማከናወንም በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በያለው ጌታነህ