ህይወት አድኖ ህይወቱን የሰዋው ዮናታን

You are currently viewing ህይወት አድኖ ህይወቱን የሰዋው ዮናታን

AMN ሰኔ 24/2017

ሰውን ከአደጋ መታደግ ነፍሱ አጥብቃ የምትሻው ነገር ነው። የነፍሱን ጥሪ ለመመለስም በ2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት በፈቃደኝነት ለማገልገል አመለከተ፡፡

ያለ ደሞዝም ማገልገል ጀመረ፡፡

ወጣት ዮናታን ገብሩ ይባላል፡፡ የእሳትም፣ የጎርፍም፣ የተፈጥሮማ ሆነ ማንኛውም ሰው ሰራሽ አደጋ በተከሰተበት ቦታ እሱ አይታጣም፡፡

ሳይታክት ነፍስን ለማዳን ይተጋል፡፡ ይህ አብዝቶ የሚወደው ሥራው ነው፡፡ በነፃ ያገለገለበት ተቋምም የዮናታንን የተሰጠ ሰብዓዊ ተግባር ተመልክቶ የጽህፈት ቤቱ ሠራተኛ አድርጎ ቀጠረው፡፡

ወጣቱ በዚህ የህይወት መሻቱ ለበርካቶች መድረስ ችሏል፡፡ አደጋን አነፍንፎ ህይወትን መታደግ ከምንም በላይ እርካታው ነው፡፡

ላለፉት ዓመታት በዚህ መልክ ወገኑን ሲያገለግል የቆየው ወጣት ዮናታን በተመሳሳይ መልኩ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ላይ የተከሰተ አደጋ ለመከላከል በተሰማራበት ስፍራ አደጋዉን ተከላክሎ ህይወትንም አድኖ እሱ ግን ህይወቱን አጣ፡፡

በዛሬው እለት ህልፈቱን አስመልክቶ የተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች ባዘጋጁት የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽር አህመድ መሀመድ ህይወቱ ቢያልፍም ተሻጋሪ ሥራ ሠርቶ ነው ያለፈው በዚህ እንኮራበታለን ብለዋል፡፡

የዮናታንን ሥራ በተግባር ህዝብን እያገለገልን ማሳየት ይኖርብናል ያሉት ኮሚሽነሩ እንደ ተቋሙ ሙዚየም እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው ወጣት ዮናታን በሙዚየሙ የመጀመሪያው ባለታሪክ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

ታሪኩ አስተማሪና ተቋማችን የሚኮራበት በመሆኑ ሌሎችም መሰል የጀግንነት ሥራ የሰሩ የኮሚሽኑ ሠራተኞችም በቀጣይ በሙዚየሙ ለማስተማሪያነት ታሪካቸው ይቀመጣል ብለዋል፡፡

ልጄ ሀገሩን ስለሚወድ ኮርቼበታለሁ ያሉት ገና ከሀዘናቸው ያልተፅናኑት እናቱ ወ/ሮ ሙሉ ሀጎስ ናቸው፡፡

የወንድሟን ህልፈት በምትኖርበት አሜሪካ ሆና የተረዳችው ታላቅ እህቱ ወ/ሮ ሰብለ ግበሩ በበኩሏ ወንድሟ ትልቅ ራዕይ የነበረው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጡ የእሳት አደጋ መከላከል ሥልጠናዎችን ለመውስድ ብዙ ጥረት ያደርግ እንደነበር ተናግራለች፡፡

ጥረቱ ተሳክቶ በአውስትራሊያ ሀገር ሥልጠና ለመውሰድ እድሉን አግኝቶ የነበረ ቢሆንም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሥልጠናውን ማግኘት እንዳልቻለ እህቱ ተናግራለች፡፡

ይህ ሁሉ ጥረቱ በሀገሩ የተሻለ ለማገልገል ካለው ትልቅ መሻት ነውም ብላለች፡

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽ/ቤት ሃላፊዎችና ባልደረቦቹም ወጣቱ ለዚህ ሥራ የተሰጠ እና በእረፍት ሰዓቱም ጭምር አደጋ ባለበት ሥፍር ደርሶ ወገኑን የሚረዳና ከሁሉም ጋር ተግባቢ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ሥራውን አጥብቆ ከመውደዱ የተነሳ ካሜራ ገዝቶ ተቋሙን በከፈተው የዩቲዩብ ቻናሉ ላይ ተቋሙን እና የተቋሙን ሠራተኞች የየዕለት ተጋድሎ ለህዝብ ያስተዋውቅ ነበር ብለዋል፡፡

ወላጆቹን ለማጽናናት ባዘጋጁት የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት ላይ ገንዘብ በማዋጣት የአንድ ሚሊየን ብር ድጋፍ ለወላጆቹ አስረክበዋል፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review