ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና የምታደርገው ጉዞ እውን የሚሆነው ልጆቿ በተሰማሩበት መስክ በእልህ እና በትጋት መስራት ሲችሉ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የሚተላለፈውን ’’የሚሰሩ እጆች ወግ’’ የተሰኘ ፕሮግራም መክፈቻ ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚረጋገጠው ጠንክረው በሚሰሩ ልጆቿ ትጋት መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ፣ ካለንበት የኢኮኖሚ ሁኔታ በቶሎ ለመውጣት እና ሀገርን ለማሻገር እልህ እና ቁጭት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማደጋቸውን እንደምሳሌ የምንወስዳቸው የዓለማችን ሀገራትም በዚሁ መንገድ ማለፋቸውን በመጥቀስ፣ በሀገራችን ስንፍና ነውር መሆኑን ደጋግመን ማስገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ስራ ማማረጥ እና ለጊዜ ያለን ትርጉምም መቀየር ይኖርበታል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ኃላፊነት የወሰደበት ይህ ’’የሚሰሩ እጆች ወግ’’ የቴሌቪዥን ፕሮግራም እውን እንዲሆን የተጉትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡
ለአንድ ዓመት በጣቢያው የሚተላለፈው ይህ መሰናዶ፣ በ15 ቀን አንድ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ስራ እና ክህሎት ቢሮ እና አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ትብብር የሚቀርብ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በመክፈቻ ዝግጅቱ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር፣ የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሞፈሪሃት ካሚል፣ ስራ ፈጣሪዎች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተካፋይ ሆነዋል፡፡
በአፈወርቅ አለሙ