በማዕከላዊ ቴክሳስ በደረሰው የጎርፍ አደጋ የሟቾች ቁጥር መጨመሩ ተነግሯል።
በዚህም እስካሁን 43 ሰዎች መሞታቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 15ቱ ህፃናት ናቸው።
አርብ ዕለት የተከሰተው ጎርፍ በአውሮፓውያኑ በ1987 በደቡባዊ ክር ካውንቲ በምትገኘው ኮምፎርት ከተማ አጠገብ በሚገኝ ቤተክርስቲያን ካምፕ አስር ታዳጊዎችን ከገደለው ጎርፍ የከፋ እንደሆነም ተነግሯል።
አደጋው ከተከሰተ አንስቶ የነፍስ አድን እና ከአካባቢው ሰዎችን የማስወጣት ሥራ እንደቀጠለ ሲሆን በግዛቷ ተጨማሪ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቂያዎች እየተሰጡ ነው።
ከአደጋው በኋላ በህይወት የተረፉትን ለማፈላለግም በርካታ የነፍስ አድን ባለሙያዎች ተሰማርተዋል።
አደጋው የተከሰተበት የከር ካውንቲ ሸሪፋ ግዛት አስተዳዳሪ ላሪ ሊታ “ሁሉም ሰው እስኪገኝ ድረስ የህይወት አድን ስራው ይቀጥላል” ሲሉ ቃል ገብተዋል።
በክር ካውንቲ የሕግ አስፈፃሚ (የሸሪፍ) መሥሪያ ቤትም በርካታ የጎርፍ አደጋዎች መከሰታቸውን ገልጾ፣ በዚህም በርካታ ሰዎች መጥፋታቸውን እና ሕይወት መጥፋቱን አረጋግጧል።
ሁለተኛ ቀኑን በያዘው የነፍስ አድን ስራ እስካሁን ወደ 850 የሚጠጉ ሰዎችን ማትረፍ መቻሉም ተገልጿል።
የጎርፍ አደጋው መንስዔ ግዛቷ በበርካታ ወራት የምታገኘው የዝናብ መጠን በጥቂት ሰዓታት ውስጥ መዝነቡ እንደሆነ ዘገባው አመላክቷል።
ጎርፉ ድልድዮችን ጠራርጎ ሲወስድ እና በከፍተኛ ፍጥነት የሚጓዝ ጎርፍ መንገዶችን ሲያጥለቀልቅ በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩ ምስሎች ማሳየታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በማዕከላዊዋ የቴክሳስ ግዛቶች ተጨማሪ የጎርፍ አደጋ ስጋቶች በመኖራቸው የማስጠንቀቂያ ደውል እየተሰማ መሆኑም ተገልጿል።